የአፋር ክልል ለህዳሴ ግድብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

59

ሰመራ ኢዜአ መጋቢት 27 /2012 ዓም የህዳሴ ግድብ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ህብረተሰቡ የጀመረዉን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ ጥሪ አቀረቡ ።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበትን 9ኛው ዓመት ምክንያት በማድረግ ትናንት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የቦንድ ግዥ አከናውነዋል ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በስነስርአቱ ላይ እንደተናገሩት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መላው ህዝብ የአመለካከት ልዩነቶች ሳይገድቡት ባደረገው ርብርብ በአሁኑ ሰአት ግንባታው ከ72 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል

የአፋር ክልል ህዝብና መንግሰትም ከሌሎች ኢትዮጵያውያኖች ጋር በመሆን ግንባታውን እስኪጠናቀቅ ድጋፍ ለመስጠት በገባው ቃል መሰረት እስከ አሁን ድረስ ከ138 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በቦንድ ግዥና በስጦታ ማበርከቱን ገልፀዋል ።

የክልሉ መንግሰትና ህዝብ ከኮሮና ቫይረስ መከላከል ስራዎች ጎን ለጎን የህዳሴ ግድብ ግንባታ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ለአፋታም እንኳን እንዳይቆም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል ።

በክልሉ የቦንድ ሽያጭ ሳምንት ትናንት በይፋ ሲጀመር ርእሰ መስተዳድሩ ለግድቡ ግንባታ የ5 ሺህ ብር ቦንድ ግዥ አከናውነዋል ።

የግል ባለሃብቱ፤ የመንግሰት ሰራተኛውንና ሁሉም የህብረተሰቡ ክፍል ለግድቡ ግንባታ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ አንዲቀጥል አመራሩ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አስገንዝበዋል ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡስማን መሃመድ በበኩላቸው  የህዳሴ ግድብ  ግንባታን ማስቀጠልና ህብረተሰባችንን ከኮሮና ቫይረስ የመከላከል ጉዳይ የሀገርን ህልውና የማስቀጠል ጉዳይ በመሆኑ ተነጣጥለው ሊታዩ የማይችሉ ናቸው ብለዋል ።

ህብረተሰቡ እራሱን ከኮሮና ቫይረስ አጋላጭ ሁኔታዎች እየጠበቀ ሀገራዊ የድህነት ትግሉን በድል ለማጠናቀቅ የሚያስችለውን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማፋጠን እንዲረባረብ ጠይቀዋል ።

የክልሉ እስልምና ጉዳዩች ፕሬዚዳንት ሼክ መሃመድ ደርሳ አንዳሉት ደግሞ ሀገራችን የተፈጥሮ ሃብቷን አልምታ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት እንዲሳካ ሀብረተሰቡ የጀመረውን ጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ገልጸዋል ።

የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ኡስማን ጠሃ እንደተናገሩት በክልሉ በዚህ በጀት አመት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች 10 ሚሊዮን ብር ከቦንድ ሽያጭና በስጦታ ለማሰባሰብ እየሰራ ነው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም