አራዳ ክፍለ ከተማ 8 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሰማራት ሃብት እያሰባሰበ መሆኑን አስታወቀ

70

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል ከ8 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሰማራት ሃብት እያሰባሰበ መሆኑን በአዲስ አበባ የአራዳ ክፍለ ከተማ አስታወቀ። 

ሃብት የማሰባሰብ ሥራው እየተሰራ ያለው በክፍለ ከተማው ሥር ባሉ 10 ወረዳዎች ሲሆን ከ50 በላይ የበጎ ፈቃድ አስተባባሪ ወጣቶች ስራውን ይመሩታል ተብሏል።

በዚህም ወጣቶቹ የተለያዩ የምግብና ሌሎች የቁሳቁሶስ ድጋፎችን ከህብረተሰቡ እያሰባሰቡ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የክፍለ ከተማው ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ አበበች እሸቴ እንዳሉት፤ በወጣቶቹ የሚሰበሰበው ሀብት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የኑሮ ጫና ለሚገጥማቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ይውላል፡፡

በኢትዮጵያ የቫይረሱን ስርጭት በቀላሉ መቆጣጠር ከተቻለም በክፍለ ከተማው ለሚገኙ አነስተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡

በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከፍተኛ ሃብት ማሰባሰብ መቻሉን የጠቆሙት ወይዘሮ አበበች፤ ባለሃብቶችና ህብረተሰቡ የጀመሩትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መንግስቱ ግዛው በበኩላቸው የኮሮቫይረስ በአገሪቱ ከተከሰተ ጀምሮ በክፍለ ከተማው የሚገኙት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የምግብና ንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን ማሰባሰባቸውን ተናግረዋል፡፡

በአራት ኪሎ አደባባይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ከመስጠት ባለፈ የንጽህና አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን የተናገረው ደግሞ በጎ ፈቃደኛ ወጣት አብይ ይሁኔ ነው።  

ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ያሰባሰቧቸውን እንደ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ፍራሽና የመሳሰሉት የምግብና ሌሎች የንጽህና መጠበቂያ ድጋፎች ለክፍለ ከተማው ማስረከባቸውን አስረድቷል፡፡

የጀመሩት መልካም ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ህብረተሰቡ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል እያደረገ ያለውን እገዛ እንዲያጠናክር ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም