በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሮናን መከላከል ላይ መዘናጋት እየታየ ነው

50

አሶሳ ፣ መጋቢት 26 / 2012 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገው የፋይናንስና የቁሳቁስ ድጋፍ እየተጠናከረ ቢመጣም በህብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት እየታየ መሆኑን የበሽታው መከላከል ግብረ ሃይል ገለፀ ፡፡

በክልሉ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ሃይል  የሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን ኮሚቴ አባል አቶ መለሰ በየነ እንደገለፁት በቅርቡ የርዕሰ መስተዳድሩ ካቢኔ አባላት የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለበሽታው መከላከል እንዲውል ወስነዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ሠራተኞች ድጋፋውን እንዲያደርጉ የማወያየት ሥራ እየተካሄደ ይገኛልም ብለዋል፡፡

በአሶሳ ከተማ የባምቡ ፓራዳይዝ 20 ሺህ ብር ጨምሮ ሆቴላቸውን በበሽታው መከላከል ስራ ለተሰማሩ  ነርሶች ማረፊያ እንዲሆን አበርክተዋል ።

ብሌንዳና ሆቴል መኪና ፣ እረቅያ ክሊኒክ 15 የመኝታ ክፍሎችና ሶስት መኪኖች ለቨይረሱ መከላከል ስራ እንዲውል ወስነዋል ።

በአሶሳ ከተማ የባምቡ ቀርከሃ ፋብሪካ ባለቤት ደግሞ በፋብሪካው ጊቢ የሚገኙ ቢሮዎችና የውሃ ማመላለሻ ቦቲ ተሽከርካሪ  ለዚሁ ሥራ እንዲውል ሲወስኑ ሃሩሜላ እና አፍሪካ ሆቴሎችም በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ የሚሄድ ከሆነ ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ባለሃብቶቹ  ቃል ገብተዋል ፡፡ 

ሆኖም ግን ህብረተሰቡ በሽታውን እንዲከላከል ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ትምህርት ቢሰጥም  በአተገባበር ላይ መዘናጋት እየታየ በመሆኑ ሊታረም እንደሚገባው አቶ መለሰ ተናግረዋል ።

ማህበራዊ ርቀትን አለመጠበቅ፣ በመኖሪያ ቤት ከመቀመጥ ይልቅ ያለምክንያት መንቀሳቀስና መሰል መዘናጋቶች እንደሚታዩ በአብነት ጠቅሰዋል፡፡

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የወጡ ድንጋጌዎችን የሚያስተገብር በርዕሰ መስተዳድሩ የሚመራ ልዩ አስገዳጅ ግብረ ሃይል መዘናጋቱን መልክ ለማስያዝ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድተዋል ።

ህብረተሰቡ ከመቼውም በላይ ጥንቃቄ በማድረግ ግብረሃይሉ በሽታውን ለመከላከል ለሚያደርገው ጥረት የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ  አቶ መለሰ ጥሪ አቅርበዋል፡፡