ኮሮናን ለመከላከል የተላለፉ ውሳኔዎችን በማይተገብሩ አካላት እርምጃ ይወሰዳል

98

ጋምቤላ ፣መቀሌ፣  መጋቢት 26 ቀን 2012 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የኮሮና ቫይረሰን ለመከላከል የተላለፉት ውሳኔዎችን በማይተገብሩ አካላት ላይ የፀጥታ ኃይሉ የተጠናከረ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሳሰቡ።

በክልሉ ከመጋቢት 23 ቀን 2012 ዓም  ጀምሮ ለ14 ቀናት እንዲተገበሩ የተላለፉት ውሳኔዎች አፈፃፀም  በተመለከተ ትናንት በአብይ ኮሚቴው ተገምግሟል።

ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የክልሉ መንግስት ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች በማይፈጽሙ አካላት ላይ የቴክኒክ ኮሚቴውና የጸጥታ ኃይሉ አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስዱ ይገባል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የህዝብ መተፋፈግ የሚታይባቸው የአገልገሎት ዘርፎችና የጠረፍ አካባቢ ዝውውሮች ላልተወሰ ጊዜ እንዲቋረጥ ውሳኔ የተላለፈ ቢሆንም አልፍ አልፎ የአፈፃፀም ክፍቶች እየታዩ ነው ብለዋል።

በተለይም በሞተር ሳይከል ትራንሰፖርት፣ በጭፈራ ፣በመጠጥ ቤቶችና በጠረፍ መግቢያና መውጫ በሮች አካባቢ የአፈፃፀም ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም በእነዚህ ዘርፎች የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል የጸጥታ ኃይሉና የዘርፉ የቴክኒክ ኮሚቴ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል።

እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር የቫረሱን ስርጭት ለመከላከል ለተጀመረው ስራ ሀብት ስለሚስፈልግ የተቋቋመው ግብር ኃይል ፈጥኖ ወደ ሀብት ማፈላለግ  ስራ እንዲገባም አቅጣጫ አስቀምጠዋል ።

ተጨማሪም አንዳንድ ያልተገባ ትርፍና ጥቅም ለማግኘት በሚንቀሳቀሱ የንግድ ማህበረሰብ ላይ የተጀመረው የክተትልና ቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ርዕሰ መስተዳደሩ ተናግረዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ካን ጋልዋክ በበኩላቸው ቫይረሱን ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የለይቶ ማቆያና የጤና ባለሙያዎች ከማዘጋጀት አኳያ ቢሮው የተቻለውን ሁሉ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ ክልሉ ሰፊ የድንበር ወሰንና ከፍተኛ የሰደተኛ ቁጥር ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ክፍተቶች መኖራቸውን ገልፀዋል ።

በመሆኑም የክልሉን የአደጋ ተጋላጭነት ታሳቢ በማድረግ በየዘርፉ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ያለመታከት እንዲሰራ የቢሮው ኃላፊ ጥሪ አቅርበዋል።   

በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ የሃይማኖት ጥምረት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ከሃይማኖት መሪዎች የሚተላለፉ መልእክቶች እንዲከበሩና እንዲተገበሩ አሳስቧል ።

የጥምረቱ አመራርና የንኡስ ግብረ ሃይሉ ሰብሳቢ ሐጅ መሓመድ ካሕሳይ እንደገለጹት አስከፊውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትለመከላከል ምእመናን በቤታቸው ሆነው እንዲፀልዩና ፈጣሪያቸውን እንዲለምኑ መክረዋል ።

‘’ወደ እምነትተቋማትለጊዜው አለመሄድ እምነትን መካድ አይደለም ’’  ያሉት  ሐጅ መሓመድ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አለመሰባሰብ አንዱ መሳሪያ ነው ብለዋል።

የበሽታውን ወረርሽኝለመከላከል በክልሉ የሚገኙ ሁሉም መስጊዶች ትላንት አርብ እለት ተዘግተው መዋላቸውን አብነት በመጥቀስ ተናግረዋል።

የጥምረቱ ፀሃፊና የመቐለ ሃገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ሃመልማል ገብረዮውሃንስ በበኩላቸው  የበሽታውን  ስርጭት እስኪገታ  ድረስ  ምእመናን  በቤታቸው ሆነው አምላካቸውን እንዲማፀኑ ጠይቀዋል ።