በአዲስ አበባ በህገ-ወጥ መንገድ ልዩ ልዩ የፍጆታ እቃዎችን ያከማቹ ግለሰቦች ተያዙ

71

መጋቢት 26/2012(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የጎሮ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረገው ክትትል በህገ-ወጥ መንገድ የፍጆታ እቃዎችን ያከማቹ ግለሰቦች  መያዛቸው ተገልጿል፡፡


የአካባቢው ፖሊስ መጋቢት 25 ቀን 2012 ዓ/ም ከወረዳ 9 ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ፅህፈት ቤት ጋር በመሆን መንግስት ለህብረተሰቡ በድጎማ የሚያቀርባቸውን ሸቀጦች በህገ-ወጥ መንገድ የሚያከማቹ ግለሰቦች ላይ ክትትል አድርጓል።

በክትትሉም ጎሮ ሰፈራ አደባባይ አካባቢ የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ  በባለ 20 ሊትር  30  እና 60 ባለ 5 ሊትር ዘይት ፣አራት ኩንታል ስኳር፣አርባ ከቀረጢት መኮሮኒ እና ሌሎች ሸቀጦችን መያዝ ተችሏል፡፡

 በተመሳሳይ መጋቢት 26 ቀን 2012 ዓ/ም በወረዳ 9 ስላሴ ማዞሪያ በአንድ መኖሪያ ግቢ ውስጥ 223 ካርቶን ባለ 5 ሊትር ዘይት መያዙን የወረዳው ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አለማየሁ ገልፀዋል፡፡

ዘይትና ስኳሩ በልዩ ልዩ ህገ-ወጥ መንገዶች ከሸማቾች ማህበር የተሰብሰቡ መሆኑን ኃላፊው ጨምረው ገለፀዋል፡፡

መንግስት እና ህዝብ በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየሰሩ ባለበት ወቅት አንዳንድ ግለሰቦች ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ሆንብለው የፍጆታ እቃዎችን እያከማቹ መሆኑን የእነዚህ ግለሰቦች ድርጊት ጥሩ ማሳያ ነው ያሉት የወረዳ 9 ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ከድር አደም በሀገሪቱ ላይ የተጋረጠውን ችግር በጋራ እና በመተሳሰብ ልንሻገረው ይገባል ብለዋል፡፡

ዋና ሳጅን ወርቅነህ አማረ በበኩላቸው የፍጆታ ዕቃዎቹ ያላግባብ በግለሰቦች እንደተከማቸ ማህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ መያዙን ተናግረው የህብረተሰቡ ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል በማለት መልዕክማስተላለፋቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም