የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ሊቋቋም ነው

75

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2012(ኢዜአ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኤካ ኮተቤ ሆስፒታልን ለማቋቋም የቀረበለትን ረቂቅ ደንብ አጸደቀ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት 81ኛ መደበኛ ስብሰባውን በቪዲዮ ኮንፍረንስ ያካሄደ ሲሆን በሁለት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም መሰረት በመጀመሪያ ምክር ቤቱ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘውን የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ሆስፒታሉ እንዲቋቋም ውሳኔ አሳልፏል።

ሆስፒታሉ የተቀናጀ፣ ጥራቱን የጠበቀ፣ የተገልጋይ ተደራሽነት ያለዉ የአዕምሮ እና የአካል ሕክምና አገልግሎቶችን አቀናጅቶ የሚሰጥ ሆኖ እንዲቋቋም ነው የተወሰነው።

ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የኤሌክትሮኒክ ግብይትን ለመደንገግ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ውሳኔ አሳልፏል።

የኤሌክትሮኒክ ንግድና የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት አገልግሎቶች የዲጂታል ኢኮኖሚው አካል መሆናቸውን መነሻ በማድረግ ረቂቁ መዘጋጀቱ ተጠቅሷል።

በመሆኑም አገሪቱ እነዚህን ዘርፎች የምትመራበት የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት በማስፈለጉ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ረቂቅ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቧል።

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል አዋጁ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም