4 ባለሀብቶች ለለይቶ ማቆያ አገልግሎት እንዲውሉ 185 አልጋዎች ያላቸው ሕንፃዎች ድጋፍ አደረጉ

86

ሐዋሳ /ሆሳእና መጋቢት 26/2012 (ኢዜአ) በሀዋሳና ሆሳእና ከተሞች የሚገኙ አራት ባለሃብቶች የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ለለይቶ ማቆያና ለህክምና አገልግሎት እንዲውሉ 185 አልጋዎች ያላቸው ህንፃዎቻቸውን አስረከቡ። 

ከሀዋሳ ከተማ ባለሃብቶች መካከል  ፓስተር ውዲቱ  ፀጋዬ የወንደር  ላንድ አካዳሚ  እህት ድርጅት አካል የሆነውንና ከ60 በላይ አልጋዎች ያሉትን የህክምና ተቋማቸውን ለለይቶ ማቆያና ህክምና አገልግሎት እንዲውል ለከተማ አስተዳደሩ አስረክበዋል ።

በአሁን ወቅት የዓለም ተግዳሮት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል ከመንግስትና ከህዝብ ጎን ለመቆም በማሰብ ተቋማቸውን ለመስጠት መወሰናቸውን ፓስተር ውዲቱ ገልፀዋል ።

አስፈላጊ ሆኖ ከተገኝ በከተማው ውስጥ ያላቸውን የእንግዳ ማረፊያና ሌሎች ድጋፎችንም ለመስጠትም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ሌላው የዱካሌ እንግዳ ማረፊያ ሥራ አስኪያጅ ወጣት ሻሻሞዱ ካሌ በበኩሉ ቤተሰቡ ተመካክሮ 50 አልጋዎች ያሉት የእንግዳ ማረፊያ ለኮሮና ቫይረስ መከላከል አገልግሎት እንዲውል መወሰኑን ተናግሯል ።

ሁሉም ሰው በዚህ ጉዳይ ላይ ባለው አቅም ሊረባረብ ይገባል ያለው ወጣቱ ቤተሰቡ ያደረገው ድጋፍ ሀገራዊ ግዴታውን ለመወጣት ሲባል መሆኑን አስረድቷል ።

በሀዋሳ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን  መምሪያ ኃላፊ አቶ መልካሙ  ወርቁ  እንደገለፁት የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ከተጀመረበት ዕለት አንስቶ በርካታ የከተማዋ ባለሀብቶች በገንዘብና በቁሳቁስ የሚበረታታ ድጋፍ አድርገዋል ።

ባለሀብቶች ካደረጉት ድጋፍ መካከል 320 አልጋዎች ያላቸው ለለይቶ ማቆያ የሚውሉ ሕንፃዎችና አንድ ለህክምና አገልግሎት የሚሆን ተቋም ይገኝበታል ።

ከዚህ ባሻገርን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ጊቢ ለሁለት ሺህ ሰዎች አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ አምስት ሕንፃዎች ለዚህ አላማ ዝግጁ መደረጋቸውን አመልክተዋል።

በጥሬ ገንዘብም እስከ አሁን ድረስ ከአራት ሚሊዮን  ብር በላይ መሰብሰብ  መቻሉን  አክለው ገልጸዋል።

 ይህ በእንዲህ እንዳለ በሃዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ የሚገኙ ሁለት ባለሃብቶችም 75 አልጋዎች ያላቸው ህንፃዎች ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ አገልግሎት እንዲሰጡ ለመንግስት አስረክበዋል ።

አቶ ኤርኪቦ ባቾሬ የተባሉ ባለሃብት በስማቸው የሚጠራውና 42 አልጋዎች ያለው ኢንተርናሽናል ሆቴል ሲያስረክቡ አቶ እንዳለ ሺሾሬ የተባሉ ባለሃብት ደግሞ 33 አልጋዎች የያዘ የእንግዳ ማረፊያ ለለይቶ ማቆያ አገልግሎት እንዲሰጥ ሰጥተዋል ።

ባለሃብቶቹ ለወደፊቱም ቫይረሱን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

የሃድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ ህንፃዎቹን በተረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት በሃገሪቱ የተከሰተውን ወረርሽን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የመንግስትን ጥሪ በመቀበል አፋጣኝ ምላሽ በመስጠታቸው  ባለሀብቶችን አመስግነዋል።

ባለሀብቶቹ የወገን ጉዳይ በማስበለጥ በራሳቸው ፍላጎት ህንፃዎቹ ለበጎ ዓላማ እንዲውሉ ማስረከባቸው ለሌሎችም አርአያነቱ የጎላ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም