ከዳያስፖራ ወገኖች እስካሁን ድረስ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደርጓል ... ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

53

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2012( ኢዜአ) በውጭ አገሮች ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ወገኖች እስካሁን ድረስ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ መደረጉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክረታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደገለጹት፤ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት መዘናጋት ከታየ የከፋ ጉዳት ሊደርስ ይችላል።

መዘናጋቱ እንዳይኖር ወረርሽኙን ምክንያት በማድረግ የተላለፉ ውሳኔዎችን የማስከበር እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የተላለፉ ውሳኔዎችን የሚያዛንፉ ተግባራትን ለማስተካከል ጥብቅ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነም ገልጸዋል።

የሃይማኖት ተቋማት ወረርሽኙን ለመከላከል በሚል ያሳለፉት ውሳኔ ላይ የሚታየውን የህግ ጥሰት ለመከላከል ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።

የተላለፉ ውሳኔዎችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ መሻሻል ቢኖርም፤ ታክሲ፣ ባጃጅ እና መገበያያ ስፍራዎች ላይ አሁንም የጥንቃቄ ጉድለት እንዳለ አመልክተዋል።

የኮሮናቫይረስ ምናልባት የከፋ ጉዳት ቢያደርስ እንኳን ለመከላከል የጸጥታ መዋቅሩ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸው፤

የጸጥታ መዋቅሩ የሚያደርጋቸውን ቅድመ ዝግጅቶች ሁሉም ህብረተሰብ እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በህብረተሰቡ መካከል ያለው መደጋገፍ የሚደነቅና የሚመሰገን መሆኑን የገለጹት አቶ ንጉሱ፤ በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ወገኖች እስካሁን ኮቪድ-19ን ለመከላከል የተደረገው ድጋፍ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር መድረሱን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ የተለያዩ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና ተቋማት ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም