ከንክኪ ነጻ ሆኖ በሰዓት ከ1 ሺህ በላይ ሰዎችን የሚያስታጥብ የጋራ እጅ መታጠቢያ ፈጠራ ለአገልግሎት በቃ

529

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2012 ከንክኪ ነጻ ሆኖ በሰዓት 1 ሺህ 200 ሰዎችን ማስታጠብ የሚችል አውቶማቲክ የጋራ እጅ መታጠቢያ የሰራው ወጣት ፈጠራውን ለአገልግሎት አበቃ።

የተለያዩ የፈጠራ ባለሙያዎች ኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19)ን ለመከላከል የሚያስችሉ የፈጠራ ሥራዎችን ወደ ተግባር መለውጥ ቀጥለዋል።

በዛሬው ዕለትም አንድ ወጣት የፈጠራ ባለሙያ የሰራውን ከንክኪ ነጻ የሆነ አውቶማቲክ የጋራ እጅ መታጠቢያ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ አገልግሎት አስጀመሯል።

የፈጠራ ባለሙያው ታምሩ ካሳ የእጅ መታጠቢያ ፈጠራውን ለመስራት ያነሳሳው የኢትዮጵያዊያን የእጅ አስተጣጠብ ባህል ሲሆን ስራውን የጀመረው ኮሮናቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመከሰቱ ቀደም ብሎ መሆኑን ለኢዜአ ገልጿል።

በኤሌክትሪክ የሚሰራው የእጅ መታጠቢያ ፈጠራው የሰዎችን እንቅስቃሴ በማንበብ የሚሰራ ሲሆን በተለይም ሰዎች በሚበዙባቸው አካባቢዎች አዋጭ እንደሆነ ይናገራል።

መታጠቢያው በተቃራኒ አቅጣጫ በአንድ ሜትር ልዩነት የተቀመጡ በአጠቃላይ አስር ቧንቧዎች የተዘጋጁለት ሲሆን በሰዓት 1 ሺህ 200 ሰዎችን ማስታጠብ የሚችል ባለ1ሺህ ሊትር የውሃ ታንከር ተገጥሞለታል።

ቴክኖሎጂው ከሌሎች የጎዳና ላይ ማስታጠቢያዎች የሚለየው የሚታጠቡት ሰዎች ካለምንም ንክኪ በተቀመጠው ሳሙና ተጠቅመው ይታጠባሉ፤ ቧንቧዎችም ያለምንም ማቋረጥ ለአንድ ደቂቃ በመፍሰስ ያስታጥባሉ።

የሚፈሰው ውሃም ፈሳሽ ቆሻሻ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ውስጥ የሚገባ በመሆኑ ከአካባቢ ብክለት የጸዳ መሆኑን ወጣቱ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ ሊግ አባል መሆኑን የገለፀው የፈጠራ ባለሙያው፤ አባላቱ ቴክኖሎጂውን ለመስራት የእውቀትና የጉልበት ድጋፍ እንዳደረጉለት ገልጿል።

ፈጠራውን ለአልግሎት ለማብቃትም እስከ 70 ሺህ ብር የሚገመት ገንዘብ ወጭ ማድረጉን አስታውቋል።

በቀጣይም የእጅ መታጠቢያ ፈጠራው ከብክለትና ከንክኪ ነጻ በመሆኑ ሰዎች በሚበዙባቸው ስፍራዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ከመንግስትም ሆነ ከሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲደረግለት ጠይቋል።