የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰቡን ከኮሮና ተጋላጭነት ለመከላከል እየሰራ ነው

416

ጎባ ፣ መጋቢት 26/2012 (ኢዜአ) በባሌ ዞን ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በመተግበር ረገድ የሚታየው ቸልተኝነትን ለማስወገድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ፡፡

ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ማህበረሰብ የኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶክተር አህመድ ከሊል ለኢዜአ እንደገለጹት ህብረተሰቡ በመንግስትና በጤና ባለሙዎች የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በተወሰነ መልኩ እየተገበረ ቢሆንም ከወረርሽኙ ስጋት አንጻር አሁንም ቸልተኝነት ይስተዋላል፡፡ 

ይህን ቸልተኝነት ለማስወገድ ዩኒቨርሲቲው በተለይ በዞኑ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ይሆናሉ ተብሎ በተገመቱ ስምንት የገጠር ወረዳዎች ውስጥ ዘላቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት ላይ ነን ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ አማራጮች እየተሰጡ ከሚገኙት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች መካከል የበሽታው ምንነት፣የመተላለፊያ መንገዱና መደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ የመሳሰሉ ይገኙበታል ።

ዶክተር አህመድ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡን የግንዛቤ ስራ ከማሳደግ በተጓዳኝ የበሽታውን ተጋላጭነት ለመቀነስ በራሪ ወረቀቶችን መበተን ፣በራሱ ሆስፒታል ውስጥ የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር ማምረትና የባሌ ሮቤ ዋና ጊቢን ለህሙማን ማቆያ ማዕከልነት የማዘጋጀት ስራ እያከናወነ ይገኛል ።

የዩኒቨርሲቲው የኮሙኒኬሽንና የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶክተር ዘላለም ረጋሳ እንደገለጹት በሽታውን በማስመልከት በጤና ባለሙዎች እየተላለፉ የሚገኙ የጥንቃቄ መልዕክቶች በአግባቡ ተግባራዊ እየተደረጉ ባለመሆናቸው ቀጣይ ሥራ ይፈልጋል ብለዋል ።

አቶ አወል ቃሲም የተባሉ የከተማው ነዋሪ በሰጡት አስተያየት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቱ በመንግስት እየተላለፉ የሚገኙ ክልከላዎችና ጥንቃቄዎችን የሚያግዙ ናቸው ብሏል፡፡

የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በ1999 የመማር ማስተማር ስራውን  የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ20 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎችን በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ከዶክተር አህመድ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡