የኮሮናቫይረስ ምልክት የታየባቸው ግለሰቦች በነጻ የስልክ መስመር ወይም ለጤና ተቋም ብቻ ጥቆማ እንዲሰጡ ተጠየቀ

54

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ምልክት የታየባቸው ግለሰቦች በነጻ የስልክ መስመር ወይም አቅራቢያቸው ወዳለው ጤና ተቋም ብቻ በመቅረብ ጥቆማ መስጠት እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።
በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ እንደገለጹት፤ አንዳንድ ግለሰቦች በስህተት አዲስ ወደ ተከፈቱ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ማዕከል ለምርመራ እያቀኑ ነው።

ይህም ደግሞ ፈጽሞ ስህተትና ተቋሞቹ ናሙና በመቀበል ምርመራ የሚያደርጉ ማዕከላት እንጂ ቀጥታ የቫይረሱ ምልክት የታየባቸውን ግለሰቦች የሚመረምሩ እንዳልሆኑ አስረድተዋል።

ይልቁንም የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብቻ በለይቶ ማቆያ ከሚገኙት የቫይረሱ ተጠርጣሪዎች ናሙና በመውሰድ ለምርምራ ማዕከላት የሚልክ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም ማንኛውም ግለሰብ የቫይረሱ ምልክት ከታየበት በነጻ ስልክ ቁጥሮች በመደወል አልያም ደግሞ ወደ አቅራቢያቸው ጤና ተቋማት በማቅናት ብቻ ማሳወቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ይህንንም ተከትሎ በአቅራቢያቸው የሚገኙ ተቋማትም ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከተቋቋመው ኮሚቴ ጋር በመወያየት በግለሰቦቹ ሁኔታ ላይ ውሳኔ የሚሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ማንኛውም ግለሰብ የቫይረሱ ምልክት ከታየበት በሃላፊነት ስሜት ራሱ(ሷ)ን ለይቶ(ታ) በማቆየት ለጤና ተቋማት ማሳወቅ እንደሚገባውም ጠቅሰዋል።

ኅብረተሰቡ በአዲስ አበባ 8335 ወይም 952፣ በትግራይ 6244፣ በአፋር 6220፣ በአማራ 6981፣ በኦሮሚያ 6955፣ በሶማሌ 6599፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ 6016፣ በደቡብ 6929፣ በሐረሪ 6864፣ በጋምቤላ በ6184ና በድሬዳዋ 6407 ነጻ የስልክ መስመር በመጠቀም ጥቆማ መስጠት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ጎን ለጎንም ኅብረተቡ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ከጤና ሚኒስቴርና ከጤና ባለሙያዎች የሚቀርብለትን ትዕዛዞች ሙሉ በሙሉ በመፈጸም ሃላፊነቱን መወጣት እንደሚገባው አሳስበዋል።

በተለይም በሽታውን ለመከላከል እጅን በሳሙና በደንብ መታጠብና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ ''መረዳዳትና መተጋጋዝም ይገባል'' ብለዋል።  

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 35 የደረሰ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ሶስቱ ሙሉ በሙሉ አገግመዋል፤ ሁለቱ ደግሞ በጽኑ ህሙማን ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም