ባለሀብቶች ከሚያደርጉት ድጋፍ ጎን ለጎን ለሥራቸውም ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቁ

79

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2012 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባለሀብቶች የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19)ን ለመከላከል ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር ኢኮኖሚው እንዳይጎዳ ሥራቸውን በጥንቃቄ እንዲያከናውኑ ጠየቁ።

በኦሮሚያ ክልል ኮሮናቫይረስን ለመከላከል እንዲውል ዛሬ በተካሄደ የገቢ ማሰባሰብ ሥራ ብቻ 31 ሚሊዮን ብር፣ ሦስት መኪናና 200 ፍራሽ ድጋፍ ተገኝቷል።

ድጋፉን ያደረጉት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ባለሀብቶች ድጋፉን ለክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስረክበዋል።

ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ባለሀብቶቹ ከሚያደርጉት ድጋፍ በላይ የተሰማሩበትን ሥራ ቢያስቀጥሉ ክልሉን የበለጠ ይጠቅማሉ።

”በዚህ ወቅት ከገንዘብ ይልቅ የእናንተ ሥራ ላይ መሆን ነው የሚጠቅመን፤ ይህን ካደረግን ነው አገራችን በችግር ውስጥ ማለፍ የምትችለው” ብለዋል።

“ይህ ካልሆነ ግን ያለምንም ቅድም ሁኔታ ሕዝቡን ከበሽታው በላይ ረሃብ እንዲገድለው እንደመፍቀድ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ሽመልስ በቀጣይም ነገሮች ከተስተካከሉ የክልሉ መንግስት ከዚህ በፊት ካደረገው በበለጠ ባለሃብቶችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል።

ሌሎች ባለሃብቶች ድጋፍ ያደረጉ ባለሃብቶችን አርአያነት በመከተል ይህን ፈታኝ ወቅት ለማለፍ በሚችሉት አቅም ከሕብረተሰቡ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ዛሬ ድጋፍ ካደረጉ ባለሀብቶ መካከል አንዱ የሆኑት የኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ ባለቤት አቶ ታዲዮስ ጌታቸው ”ባለሃብቱ እንደቀድሞ በሚችለው አቅም መረዳዳት አለበት” ብለዋል።

አንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረጉት አቶ ታዲዮስ ድርጅታቸው በዚህ ወቅት ሙሉ በሙሉ ሥራ ያቆመ ቢሆንም ችግሩን ለመወጣት በጋራ መተጋገዝ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ሌሎች ባለሃብቶችም በሚችሉት አቅም ከሕዝቡ ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል።

ሌላው የቤካስ ኬሚካል ኢንዱስትሪ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ በቀለ ጸጋዬ ለክልሉ መንግስት የ500 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።

እሳቸውም እንደ አቶ ታዲዎስ ሁሉ “የሁሉም መረዳዳት ጠቃሚ ቢሆንም ባለሃብቱ ድጋፉን ሊያጠናክር ይገባል” ብለዋል።

ድርጅታቸው የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ አምራች በመሆኑ አቅሙን በማሳደግ በስፋት እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

በመጀመሪያ ዙር የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ወደ 46 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ለክልሉ መንግስት ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ማስረከባቸው ይታወቃል።