የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ህገወጥ ተግባር የፈጸሙ 424 ነጋዴዎች በእስራት ተቀጡ

446

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2012( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ህገወጥ ተግባር የፈጸሙ 424 ነጋዴዎች በእስር መቀጣታቸውን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስትሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ በወረርሽኙ ምክንያት በአገር ደረጃ በምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የሚሰራ አገር አቀፍ ግብረሃይል መቋቋሙን አውስተዋል።  

”እስካሁን በአጠቃላይ የማገድ፣ የማሸግ፣ ፈቃድ የመሰረዝና የእስር ቅጣትን ጨምሮ ከ15 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማትና ድርጅቶች ላይ ርምጃ ተወስዷል” ብለዋል።

ከነዚህ ውስጥ በምርት ላይ ባዕድ ነገር በመቀላቀል፣ ያለአግባብ ምርት በማከማቸትና ሌሎች ችግሮችን የፈጠሩ 424 ነጋዴዎች በእስራት መቀጣታቸውን ተናግረዋል።

ተቋማቱ በርበሬ ላይ ቀይ አፈር በመጨመር፣ ቅቤ ላይ ባዕድ ነገር በመቀላቀልና ንጽህና መጠበቂያ አልኮልን ከውሃ ጋር ቀላቅሎ በማቅረብ ህገ-ወጥ ተግባር የፈጸሙ ናቸው።

በቀጣይም ከምርቶች ጋር ባዕድ ነገር የሚቀላቅሉ፣ ገበያውን የሚያውኩ፣ ምርት የሚያከማቹና ሌሎች ህገ-ወጥ ተግባራትን የሚፈጽሙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃው እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

መንግስት እንደ አስፈላጊነቱ ገበያውን የማረጋጋት ስራ የሚያከናውን መሆኑን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ ህገወጥ ተግባራት የሚፈጽሙ ነጋዴዎችን እንዲያጋልጥ ጥሪ አቅርበዋል።

ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች  ምርት በድጎማ  እየቀረበ እንደሆነም ገልጸዋል።

በዚህም ስንዴ 648 ሺህ ኩንታል፣ ስኳር 615 ሺህ ኩንታል እንዲሁም 40 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በየወሩ ሳይቋረጥ እየቀረበ እንደሆነ አመልክተዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ከውጭ እስኪገባ የስንዴ አቅርቦት እጥረ እንዳይፈጠር 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በብድር ተወስዷል።

ገበያውን እንዲያረጋጋ በተቋቋመው የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን 900 ሺህ ኩንታል በቆሎ መኖሩንም ጠቅሰዋል።

በአገር ደረጃ አትክልት 8 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል፣ ፍራፍሬ 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል፣ ስራስር 45 ሚሊዮን ኩንታል፣ ቆጮ 38 ሚሊዮን ኩንታል መኖሩን የግብርና ሚኒስቴር መረጃን ጠቅሰው አብራርተዋል።

በመሆኑም በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የምርት እጥረት እንዳለ አስመስለው ገበያውን የሚያውኩ ነጋዴዎችን መንግስት እንደማይታገስ አስጠንቅቀዋል።

”በኮሮናቫይረስ ምክንያት አላስፈላጊ የዋጋ ንረት እንዳይመጣና ህብረተሰቡ የሸቀጥ እጥረት እንዳያጋጥመው የዳያስፖራ አካውንት ያላቸው ዜጎች እንዲሁም አለም አቀፍ ኩባንያዎች የምግብ ሸቀጦችን እንዲያስመጡ እየተሰራ ነው” ብለዋል።