የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የግሉን ና የመንግስትን ቅንጅት እንደሚጠይቅ ተገለጸ

74

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የግሉን ዘርፍና የመንግስትን የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅ ገልጻል። 

ምክር ቤቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እስኪቆም ድረስ አንዳንድ መሰረታዊ የግብርና ምርቶች ወደ ውጭ እንዳይላኩና ቅድሚያ ለአገር ውስጥ ፍላጎት እንዲሰጡ አመልክቷል፡፡

የፋይናንስ ተቋማት ማለትም ባንኮች ለግሉ ዘርፍ የሰጡትንና የሚሰጡትን የብድር ወለድ ምጣኔ እንደ አግባብነቱ ክለሳ እንዲያደርጉ ጠቁሟል፡፡

በሂደቱም ወደ ኢኮኖሚው የሚገባው ማንኛውንም የገንዘብ መጠን የዋጋ ግሽበትን እንዳያባብስ ክትትልና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

መንግስት ከግሉ ዘርፍ ጋር ሆኖ ለምግብ እና ግብርና ምርቶች ማሰራጫ ማዕከላትን በተጠኑ አማካይ ስፍራዎች ላይ እንዲከፈተት የጠቆመው መግለጫው፣ ህብረተሰቡም በአስተማማኝ ሁኔታ ምርቶቹን እንዲያገኝ ማስቻል እንደሚገባም ገልጿል፡፡

የግል ቀጣሪ ድርጅቶች ሊፈጠር በሚችል የገበያ መቀዛቀዝ ምክንያት ከአቅም በታች እንዳያመርቱና በዚህ ሳቢያም ሰራተኞቻቸውን እንዳይቀንሱ መንግስት በልዩ መመሪያ ሁኔታዎችን እንዲመቻች ጥሪ አቅርቧል፡፡

የዝቅተኛ ወርሃዊ ደመወዝ ገቢ ግብር የወለል መጠን ከፍ እንዲል በጥናት ላይ የተመሰረተ ክለሳ እንዲደረግም ነው ምክር ቤቱ የጠየቀው።

ከወረርሽኙ ለመጠበቅና ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን በማምረትና በማከፋፈል ረገድ አስተዋፅዖ ለማድረግ ቀልጣፋ ርምጃ ሊወሰድ ይገባልም ብሏል፡፡

በወረርሽኙ ሳቢያ የሚጎዱና ሊጎዱ የሚችሉ ኢንዱስትሪዎችን የግብር እፎይታ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚስፈልግ አስገንዝቧል፡፡

ለአገር ውስጥ አምራቾች ከወትሮው በተለየ መልኩ መመሪያ ወጥቶ የሚያስፈልጓቸውን ጥሬ እቃዎች በፍጥነት እንዲያስገቡ እና አስፈላጊ ምርቶች በፍጥነት ለተጎጂዎች እንዲዳረስ ማድረግ እንደሚገባም ገልጿል፡፡

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ምርታቸውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ኩባንያዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩና ምርታቸውን ለአገር ውስጥ ገበያ ጭምር እንዲያቀርቡ በጊዜያዊነት የሚበረታቱበት መመሪያ ማውጣት እንደሚያስፈልግም በመግለጫው ተካቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም