አርቲስት ፀደንያ ገብረማርቆስ ህብረተሰቡ ራሱን ከኮሮናቫይረስ እንዲከላከል የጥንቃቄ መልዕክት አስተላለፈች

56

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2012( ኢዜአ) አርቲስት ፀደንያ ገብረማርቆስ ሕብረተሰቡ ራሱንና ሌላውን ወገን ከኮሮናቫይረስ እንዲከላከል በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የጥንቃቄ መልዕክት አስተላለፈች።

አርቲስቷ መነሻዋን ከሳሪስ ካዲስኮ መዳረሻዋን ደግሞ ኃይሌ ጋርመንት በማድረግ ህብረተሰቡ ራሱን ከኮሮና ቫይረስ እንዲከላከል ትናንት የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፋለች።

የጥንቃቄ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ በተዘዋወረችባቸው አካባቢዎች ህብረተሰቡ በሚፈለገው ልክ ጥንቃቄ እያደረገ እንዳልሆነ መታዘቧን ገልጻለች።

በተለይ በገበያ እና በትራንስፖርት አካባቢዎች የሰዎች መጨናነቅ በስፋት ስለሚስተዋል በመንግስት በኩል ጠበቅ ያሉ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባ ተናግራለች።

ብዙ ሰው ኑሮው በየዕለቱ በሚያገኘው ገቢ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ጠበቅ ያለ እርምጃ ሲወሰድ አቅመ ደካሞች ለተወሰኑ ጊዜ የሚደጎሙበት መንገድ መመቻቸት እንዳለበት ተናግራለች።

አርቲስት ፀደንያ እንዳለችው፤ ህብረተሰቡ በመንግስትና በጤና ባለሙያዎች የሚተላለፉ የግንዛቤ ማስጨበጫ መልእክቶችን በሚገባ መተግበር ይኖርበታል።

ከቤት የሚያስወጣ አስገዳጅ ነገር ሲገጥመውም አካላዊ ርቀቱን ጠብቆ መንቀሳቀስ እንዳለበት አስገንዝባለች።

በኮሮናቫይረስ እስከዛሬ ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የተያዙ ሲሆን ከ53 ሺህ በላይ የሚሆኑት ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን በበሽታው ማጣታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም