በጎ አድራጊዋ ቤታቸውን ለኮሮና ቫይረስ መከላከል አበረከቱ

48

ድሬዳዋ/ኢዜአ/ መጋቢት 25/2012 የድሬዳዋ ነዋሪ የሆኑ በጎ አድራጊ ባለአንድ ፎቅ ቤታቸውን ለኮሮና ቫይረስ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲያግዝ አበረከቱ። 
በሌላ በኩል በዚሁ ከተማ  ዋና ዋና ጎዳናዎችና አካባቢዎች የፀረ-ተዋህሲያን ኬሚካል  ርጭት ተካሄዷል፡፡

በጎ አድራጊዋን በመወከል ባለፎቅ ቤታቸውን ለድሬዳዋ አስተዳደር ያስረከቡት አቶ መዝገቡ ልዑለቃል ናቸው።

በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ስማቸው እንዳይገለጽ  የፈለጉት የ70 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ  ወይዘሮ ቤታቸውን ለበጎ ተግባር ያበረከቱት  አስተዳደሩ ያስተላለፈውን ጥሪ ሰምተው ለማገዝ ነው፡፡

"ቤቱ በወር 35ሺህ ብር ይከራይ እንደነበር ገልጸው በሽታውን መቆጣጠር እስኪቻል ድረስ አስተዳደሩ ቤቱን እንዲጠቀምበት ፈቅደዋል "ብለዋል፡፡

ቤቱን የተረከቡት የድሬዳዋ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስና መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ኃይል ለይቶ ማቆያና የሎጅስቲክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሮቤል ጌታቸው በጎ አድራጊዋ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።

"ቤቱ ለይቶ ማቆያ መከታተያና ማከሚያ ማዕከላት ለሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎች መኖሪያነት ያገለግላል "ብለዋል፡፡

ሌሎች ባለሃብቶችም የእሳቸውን ፈለግ ተከትለው ድጋፍ በማድረግ ቫይረሱን ለመከላከል የሚከናወነውን ተግባር እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኬሚካል ርጭቱን ያካሄዱት የከተማው ሥራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት  የድሬዳዋ ጤና ቢሮና የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን በመቀናጀት ነው።

ርጭቱ በዋና ዋና የአስፋልት መንገዶችና ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ የተካሄደ  ሲሆን በቀጣይ በሰፈሮችና በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ እንደሚቀጥል ተመልክቷል፡፡

የኬሚካል ርጭቱ በተካሄደበት ውቅት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር እንደተናገሩት፤ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡

የኬሚካል ርጭት ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል መንግስት ያስተላለፋቸውን ክልከላዎችንም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን የለውጥ ስራዎችና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ  በበኩላቸው የኬሚካል ርጭቱ እንዲሳካ ህብረተሰብ ላደረገው ትብብርና ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

አንዳንድ ግለሰቦች የተረጨውን ለመጥረግና ለማጠብ ጥረት ሲያደርጉ  እንደነበር አውስተው ከዚህ መሰል ህገ-ወጥ ድርጊት መታቀብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም