ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ የውሃ ክፍፍል ላይ መደራደር አትሻም

157

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2012( ኢዜአ) ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ወደ ውሃ ክፍፍል ድርድር የመሄድ አቋም እንደሌላት የሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ አባላት ተናገሩ።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ አለቃቀቅና ሙሌት ላይ በኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን እየተካሄደ ያለው ድርድር እስካሁን መቋጫ አላገኘም።

በድርድሩ በአባልነት እየተሳተፉ የሚገኘት አቶ ዘሪሁን አበበ በሕዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ላይ የሚካሄደው ድርድር በሙያተኞች እንዲደረግ በመሪዎች የተወሰነ ቢሆንም በግብጽ በኩል የፖለቲካና ደህንነት ጉዳይ ስታደርገው እንደሚስተዋል ነው የገለጹት።

"ጉዳዩ ያለ አግባብ የፖለቲካ ሽፋን እንዲኖረው በማድረጓ እና በማጦዟ ስምምነት ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ አድርጎታል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ የላይኛው ተፋሰስ አገር ሆና በትብበር እንስራ ብትልም ግብጽ የኢትዮጵያን የውሃ ድርሻ ዜሮ በማድረግ የቅኝ ግዛት ውሎችን የመጫን አዝማሚያ አላት።

"ይህም ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የመነጨና በቀጠናው 'እኔ ብቻ ልጠቀም አዛዥም ልሁን' ከሚል እሳቤ በመሆኑ ኢትዮጵያ ልትቀበለው አትችልም" ብለዋል አቶ ዘሪሁን።

የአባይን ውሃ 86 በመቶ ለዘመናት እየተጠቀመች ያለችው ግብፅ 479 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የናስር ሰው ሰራሽ ሃይቅ በመገንባት የተትረፈረፈ ዓሳ ታመርትበታለች።

ከአስዋን ግድብ ሃይል በማመንጨት ለዜጎቿ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ከማድረጓ በተጨማሪ ካይሮና አሌክሳንደሪያ ከተሞችም ውሃውን እንዳሻቸው ያደርጉታል።

መነሻውን ከቡሩንድና ሩዋንዳ ተራሮች ከሚያደርገው ነጭ አባይ ኡጋንዳ ግድብ በመገንባት ሃይል ታመነጭበታለች።

ሱዳንም ከናይል ውሃ የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት ግልጋሎት እያገኘች ቢሆንም ከአገሯ በሚነሳው ጥቁር አባይ ላይ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ የሃይል ማመንጫ ግንባታ መጀመሯ ግን ለግብፅ አልተዋጠላትም።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ላይ ሲደረግ የነበረው ድርድርም በግብጽ ወትዋችነት አቅጣጫውን ስቶ ወደ ውሃ ክፍፍል አምርቷል።

የውሃ ክፍፍል ጉዳይ ደግሞ በሦስቱ አገሮች ብቻ እንደማይወሰን የናይል ተፋሰስ አገራት የትብብር ስምምነት ይደነግጋል።

በትብብር ስምምነቱ መሰረት 11ዱም የናይል ተፋሰስ አገራት ውሃውን በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት አላቸው።

የሦስቱ አገሮች ብቻ የውሃ ክፍፍል ድርድር ግብጽና ሱዳን ሌሎችን ሳያካትቱ ውሃውን ለመጠቀም በ1959ን ያደረጉትን ስምምነት የሚደግም ስህተት መሆኑን አቶ ዘሪሁን ያስረዳሉ።

በየጊዜው አቋሟን የምትቀያይረው ግብጽ የመሪዎች ስምምነት መግለጫ ላይ ያልተካተተ "አባይን በበጋ እና በክረምት" በሚል ስለ ውሃው ምጣኔ እንደራደር የሚል አዲስ ሃሳብ ይዛ ብቅ ማለቷንና ይህም ኢትዮጵያን የውሃ ክፍፍል ድርድር ውስጥ የማትገባ መሆኑን ግን ባለሙያው አስረድተዋል።

ሌላው የተደራዳሪ ቡድኑ አባል ዶክተር ይልማ ስለሺ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከግድቡ ጋር ያሉ ልዩነቶችን በመፍታት ተፋሰስ አቀፍ ልማትና በትብብር የመስራት አቋም ታራምዳለች ብለዋል።

በመጨረሻው ድርድር ግብጽ ድርቅን ለመቋቋም ያቀረበችው ሀሳብ የኢትዮጵያን የውሃ መጠቀም ህልውና የሚያሳጣ በመሆኑ ውድቅ መደረጉን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የተፋሰሱን አገሮች በማይጎዳ መልኩ እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት በማድረግ በትብብር የመልማት አቋሟን ይዛ ድርድሯን እንደምትቀጥልም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያን የውሃ አጠቃቀምና የመልማት መብት ለመንጠቅ የሚደረጉ ጥረቶችን ተደራዳሪ ቡድኑ በጭራሽ እንደማይቀበለውም አስረግጠዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ዘጠኝ ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን የግንበታው ሂደትም ከ72 ነጥብ 4 በመቶ በላይ ደርሷል።


የግድቡ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ተርባይኖች በታህሳስ 2013 ዓ.ም ኃይል ማመንጨት የሚጀምሩ ሲሆን ግድቡ ሲያልቅ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የሚይዝ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም