ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ በክልሉ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከተቋቋመው ኮሚቴ ጋር ተወያዩ

53

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2012( ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከተቋቋመው ኮሚቴ ጋር በፅህፈት ቤታቸው ተወያዩ። 

የክልሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሳይዛባ ህብረተሰቡ ስለኮሮናቫይረስ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል።

በተለይ ፋብሪካዎች ሠራተኞቻቸውን ከቫይረሱ መከላከል በሚችሉበት ሁኔታ ሥራቸውን ማከናወን እንዳለባቸውም መክረዋል።

አርሶ አደሩም የልማት ሥራውን በጀመረበት መንገድ ሊቀጥል ይግባል ብለዋል።

በትራንስፖርት ዘርፍ በከተሞች ውስጥ የሚደረግ የታክሲ እንቅስቃሴ እንዲሁም ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ የሚደረግ የህዝብ ትራንስፖርት እንዲቆም መወሰኑንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቋቋመው ኮሚቴም እስካሁን ለ9 ሚሊዮን ሰዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በገጽ ለገጽ መሰጠቱን አስታውቋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጥረትም 144 ሺህ በጎ ፈቃደኞች ነፃ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ብሏል ኮሚቴው።

እስካሁን  ቫይረሱን ለመከላከል ተግባር የሚውል 46 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉም ታውቋል።

በክልሉ እስካሁን 44 የለይቶ ማቆያ ቦታዎች፣ 107 ሆስፒታሎች፣ 174 ጤና ጣቢያዎች፣ 677 አልጋዎች እና 23 አምቡላንሶች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ዝግጁ መሆናቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም