በኮሮናቫይረስ የተያዙ ስድስት ተጨማሪ ሰዎች ተገኙ

187

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 24 ሰዓት የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 74 ሰዎች ውስጥ 6 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ። 

ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 35 እንዳደረሰው የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት፤ በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡት ውስጥ አምስቱ ከአዲስ አበባ ሲሆን አንድ ከድሬዳዋ ነው።

በቫይረሱ የተያዙት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው።

በአዲስ አበባ ከተያዙት ውስጥ ሁለቱ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሲሆን የመጀመሪያው የ35 ዓመት ወንድ መጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከዱባይ የመጣ፣ ሁለተኛው የ30 ዓመት ወንድ በተመሳሳይ ከዱባይ መጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም የመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ሁለቱም አስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት የገቡ ናቸው።

ሶስተኛው የ28 አመት ወንድ፤ አራተኛውም የ56 ዓመት ወንድ፣ አምስተኛው የ30 ዓመት ወንድ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ናቸው።

እነዚህ ሰዎች ያላቸው ግንኙነት እየተጣራ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ስድስተኛዋ ሰው የ33 ዓመት ሴት ስትሆን በድሬዳዋ ከዚህ በፊት በኮሮናቫይረስ መያዙ ከተገለጸው ሰው ጋር ግንኙነት የነበራት መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም