ኮሮናን በምንከላከልበት ወቅት በሃሰተኛ መረጃ ህዝቡን ለማደናገር መሞከር ተገቢ አይደለም…የሶማሌ ክልላዊ መንግስት

206

ጅጅጋ መጋቢት 24/2012 (ኢዜአ)የሶማሌ ክልል አመራሮች የኮሮና ቫይረስን የመከላከል ስራዎችን በቅንጅት በሚያከናውኑበት ወቅት ሃሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ህዝብን ለማደናገር መሞከር ተገቢ አይደለም ሲል የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ሀቢብ ሙሁመድ በቢሯቸው ዛሬ ማምሻውን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት በክልሉ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመከላከል ሁሉም አመራር የተሳተፈበት የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የወቅቱ አሳሳቢ ጉዳይም የህዝቡን ጤናና ደህንነት መጠበቅ መሆኑን ገልጸው ለዚህም አመራሩ በተለያዩ አግባቦች በየደረጃው ህዝቡን የማንቃት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ የክልሉን ሰላም ያልተረዱ አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው አካላት በክልሉ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እንደተካሔደ በማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚያስተላልፉት ሃሰተኛ መረጃ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

“ህብረተሰቡ በተለያየ መንገድ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እያደረገ ያለውን ተግባር ለማዘናጋት ሆን ተብሎ የሚናፈስ አሉባልታ ነው” ያሉት ኃላፊው ህዝቡ በሃሰት ወሬ ሳይረበሽ የተጀመረውን የኮሮና ቫይረስ የመከላከል ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።