የጤና ሚኒስቴር እና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

80

አዲስ አበባ፣መጋቢት 24/2012 (ኢዜአ) የጤና ሚኒስቴር እና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ችግረኛ ወገኖችን መርዳት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱም በዋናነት ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር ተያይዞ በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች የንጽህና መጠበቂያ ግብዓቶችን መርዳት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ናቸው።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ የሆኑ አቅም የሌላቸው በርካታ ዜጎች አሉ።

የብልጽግና ፓርቲ በቅርቡ ተጋላጭ የሆኑ ወገኖችን ችግር ለመቅረፍ 100 ሚሊዮን ብር ለጤና ሚኒስቴር መለገሱን አስታውሰዋል።

በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረትም በሁሉም የአገሪቱ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለሚገኙ አቅመ ደካሞች ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ድጋፉን የሚያገኙ ወገኖችን ልየታ አከናውኗል ብለዋል።

ለጎዳና ተዳዳሪ ዜጎች አገልግሎት እየሰጡ ባሉ ተቋማትና በአረጋዊያን ማእከላት አማካኝነት ድጋፉ ተደራሽ እንደሚሆንም ገልጸዋል።

በተጨማሪ በአገሪቱ በሚገኙ መናኸሪያዎችና የጤና ተቋማት ላይ የንጽህና መጠበቂያ  ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም