በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከናወኑ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?

74

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2012 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ መስኮች ስኬታማ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ፅህፈት ቤቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በሁሉም ዘርፎች የመጡ ውጤቶችን በዝርዝር ለይቶ አመልክቷል።

በግብርና ዘርፍ በ12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ 329 ሚሊዮን ኩንታል ምርት  ሲገኝ የ43 ቢሊዮን ብር ግብዓት ለአርሶ አደሮች እንዲሰራጭም ተደርጓል።

በአገር ውስጥ ስንዴን ለማምረት በተጀመረው ሥራም 3 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ለማልማት ተሞክሮ በሄክታር 44 ኩንታል ተገኝቷል።

ይህ ደግሞ ከተለመደው የምርት ግኝት በ62 በመቶ ብልጫ ሲኖረው ለ1 ነጥብ 95 ሚሊዮን ዜጎች ሥራ መፍጠር አስችሏል ብሏል መግለጫው።

"በአርብቶ አደር አካባቢዎች 636 ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ መሆኑም ታውቋል"፤ በዚሁ አካባቢ 397 ሚሊዮን ዶዝ የእንስሳት ክትባትም ተመርቷል።

በሁለት ዓመታት 4 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን ያስታወሰው የጽህፈት ቤቱ መግለጫ በተያዘው ዓመት ክረምት 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን አመልክቷለ።

የሕግና አገራዊ ጉዳዮች ሲቃኙም የተለያዩ ሕጎች ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል።

የሲቪል ማሕበረሰብ ሕግ፣ አዲሱ የምርጫ ሕግ፣ የመገናኛ ብዙሃን አዲሱ ሕግና የወንጀል ስነ ስርዓት ማስረጃ ሕግ በአጠቃላይ 9 መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ሕጎች ተረቀዋል።

በምህረት አዋጁ ከ43 ሺህ 500 በላይ ግለሰቦች የተለቀቁ ሲሆን በነዚህ ዓመታት በግጭት ከተሳተፉት ውስጥ 1 ሺህ 600 ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሙስናና በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር 407 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር እንዲታገድ መደረጉም ተመልክቷል፤  2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ግምት ያለው የኮንትሮባንድ እቃም ተይዟል።

ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በአንድ ዓመት ከግማሽ 325 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉም የፋይናንስ ዘርፍ ትልቅ ስኬት ተብሎ በመግለጫው ተመልክቷል።

መንግስት ባደረገው ድርድርና ውይይት በቀጣይ አምስት ዓመታት የተወሰደው ብድር መልሶ ክፍያው በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ተደርጓል።

የጽህፈት ቤቱ መግለጫ እንደሚያሳየው በ2011 እና በ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ከ7 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ብድርና እርዳታ ተገኝቷል።

የኢትዮጵያን የከርሰ ምድር ሀብት በተመለከተም 5 ነጥብ 47 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸው አዳዲስ የማዕድን ኢንቨስትመንቶች ተመዝግበዋል።

ለነባር የነዳጅ ምርመራ ልማት ከ67 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን በዚህም ከ450 ሚሊዮን ቶን በላይ የሙከራ ነዳጅ ተሽጦ 135 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ዘርፍ አፈጻጸሙ ሲታይ በሁለቱ ዓመታት ከ23 ሺህ በላይ የገጠር መጠጥ ውሃ የተገነባበት፣ 61 የከተሞች የመጠጥ ውሃ ግንባታ የተጠናቀቀበት፣ የ21 ሰፋፊ የመስኖ ፕሮጀክቶች ዲዛይንም የተጠናቀቀባቸው ነበሩ።

ግንባታቸው የዘገዩ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከ24 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ ማልምት የተቻለበት ጊዜ እንደነበር በመግለጫው ተመልክቷል።

በሁለት ዓመታት ውስጥ 339 ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል፤ በቅርቡ የሚመረቁ ከ1 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኃይል የሚያመነጩ ፕሮጀክቶችም እየተካሄዱ ይገኛሉ።

በመንገድ ልማት ዘርፍም 4 ነጥብ 43 ሚሊዮን ብር ከመንገድ ፈንድ የተሰበሰበ ሲሆን በግንባታ ላይ ከነበሩት ፕሮጀክቶችም 46 በመቶ ያህሉ ተጠናቀዋል፤ ከ3 ሺህ 77 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድም ተገንብቷል።

በነዚህ ዓመታት የመርከብ የወደብ ቆይታ በአማካይ ከ45 ቀን ወደ 18 ዝቅ ያለ ሲሆን የአዋሽ-ወልዲያ-ሃራ ገበያ የባቡር መንግድ ሥራም 91 ነጥብ 88 በመቶ መጠናቀቁ ተመልክቷለ።

የከተሞችን የካዳስተር ስርዓት ለመተግበርም በ23 ከተሞች ተጀምሯል፤ ከ583 ሺህ በላይ ዜጎችም የከተማ የምግብ ዋስትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል።

በዲፕሎማሲ መስክም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ከ20 ዓመታት በላይ የዘለቀው ቁርሾ እልባት አግኝቷል።

በኤርትራና ጅቡቲ መካከል የነበረውን ችግር ለመፍታት የአስታራቂነት ሚናም በኢትዮጵያ በኩል ተከናውኗል።

በሱዳን ተከስቶ የነበረው የፖለቲካ ችግርም ይፈታ ዘንድ ወሳኝ ሥራ የተሰራ ሲሆን የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነትም ይተገበር ዘንድ ትልቅ ስራ ተሰርቷል።

በተለያዩ አገራት በእስር ላይ የነበሩ 29 ሺህ ዜጎች ተፈተው ወደ አገራቸው ገብተዋል፣ ከ178 ሺህ በላይ በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር የወጡ ዜጎችም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።

በባህልና ቱሪዝም መስክም የላልይበላ ውቅር አብያተ ከርስቲያናት ጥገና፣ የአባ ጅፋር ቤተ መንግስት እየተጠገነ ሲሆን የቪላ አልፋ ጥገናም ተጠናቋል።

ከጎብኚዎች አንጻር ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የውጪ ቱሪስቶች እና ከ25 ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ ቱሪስቶች ጉብኝት አድርገዋል፤ ከቱሪዝም ዘርፉም ከ4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል።

በትምህርት ዘርፍ የተገኘው ውጤት እንደሚያሳየው በ2011 ዓ.ም የትምህርት ቅበላ ከ1ኛ እስክ 8ኛ ክፍል 89 በመቶ፣ ከ9 እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ 48 በመቶ ደርሷል።

ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ተጀምሯል፤ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች ጋር በትምህርት ፍኖተ ካርታ ላይ ውይይት ተደርጓል።

በጤና ሚኒስቴር 50 በመቶ አስፈጻሚዎች ሴቶች እንዲሆኑ የተደረገ ሲሆን፤ የሕይወት አድን መድኃኒት አቅርቦትም ከ59 በመቶ ወደ 96 ነጥብ 9 በመቶ አድጓል።

በሁለት ዓመታት የ484 ጤና ጣቢያዎች ደረጃ ሲያድግ የአምስት ሆስፒታሎች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል። 1 ሺህ 753 አምቡላንሶች ተገዝተው ተሰራጭተዋል።

በማህበራዊ ዘርፍም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች የማህብራዊ ደህንነት ድጋፍ ቀጥታ ተጠቃሚ ሆነዋል።

በአገር ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጠራ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ ሲሆኑ በ8 ከተሞችም ከ6 ሺህ በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎችን የማቋቋም ሥራ እየተከናወነ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም