የለውጥ ጉዞው ከዳር እንዲደርስ ድጋፋችንን እናጠናክራለን...በባህር ዳር የድጋፍ ሰልፍ ተሳታፊዎች

104
ባህር ዳር ሰኔ 24/2010 በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ አመራርነት የተጀመረው የአንድነት፣ የፍቅርና የለውጥ ጉዞ ከዳር እንዲደርስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ። በምስጋናና በድጋፍ ሰልፉ ላይ ከተገኙት የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ፍቃዱ ሞላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሰላም፣ ለፍቅርና ለአንድነት የሰጡት ዋጋና የመጣው ለውጥ ለድጋፍ እንዲወጡ ያነሳሳቸው መሆኑን ገልጸዋል። “ለህዝቦች ነፃነትና ለእውነት የቆሙና አንድነትን ያረጋገጡ ኢትዮጵያ መሪ መሆናቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በተግባር ባከናወኗቸው ሥራዎችና ባመጧቸው ለውጦች አረጋግጠናል” ብለዋል። "በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ደምቄ የወጣሁትም ቀደምት አባቶቻችን የሞቱላትና የተዋደቁላት የተጋድሎ አርማችን በመሆኗ ነው" ሲሉም ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትክክለኛ ነጻነትና ዴሞክራሲ በአገሪቱ እንዲሰፍን ያደረጉ፣ ዕውነትን የሚሹ ሚዛናዊ ዳኛ በመሆናቸው ፈጣሪ ዕድሜና ጤናን ሰጥቶ እንዲያቆያቸው ተመኝተዋል። በቀጣይም የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ ጅማሮዎች ለማስፈፀም እንደአንድ ዜጋ ከጎናቸው ሆነው የአገሪቱን ልማት ለማፋጠን ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ለመጀመሪያ ጊዜ ዜጎች ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹና ኢትዮጵያዊነትን በማጉላታቸው  ድጋፍ መውጣቷን የገለጸችው  የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ሃብታም ጥላሁን ናት። "ዶክተር አብይ የያዙት አገራዊ ዓላማ በህዝቦች መካከል ፍቅር፣ አንድነትና መተሳሰብ እንዲጎለብት በማድረግ በኩል ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ ከግብ እንዲደርስና ዘረኝነት እንዲጠፋም ከጎናቸው ሆኜ የድርሻዬን ዕወጣሁ" ብላለች። "ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ....እየተባለ እንጂ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅን መሪ ሰምቼ አላውቅም፤ በሰልፉ ላይ ከህዝቡ ጋር ለመደመር ያወጣኝም ይሄ ነው" ያለው ደግሞ የጦር አካል ጉዳተኛ የሆነው አሥር አለቃ ምላርግህ በየነ ነው። ዶክተር አብይ አህመድ ስለአንድነትና ፍቅር ሲሰብኩ በመስማቴ አካል ጉዳተኝነቴ ሳይገድበኝ ምስጋናዬን በአደባባይ ለማቅረብና ከእሳቸው ጎን መሆኔን ለማሳየት ለሰልፍ ወጥቺያለሁ" ብሏል። ወጣት ኃይለኢየሱስ እናውጋው በበኩሉ "ዛሬ በምስጋናና ድጋፍ ሰልፉ ላይ ስንሳተፍ ከምስጋና ባለፈ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መርህ ተከትለን ያሰቡት እንዲሳካ ከጎናቸው መቆማችንን በተግባር ለመግለጽ ጭምር  ነው" ሲል ተናግሯል። በድጋፍ ሰልፉ ላይ ለኤርትራዊያን ያለውን ፍቅር ለመግለጽና በተካሄደው ጦርነት የተሰውትን ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹን ለማስታወስ ሲል  የኤርትራን ባንዲራ ይዞ አደባባይ መውጣቱን ገልጿል። ዛሬ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለድጋፍ የወጡ ሰልፈኞች ከያዟቸው መፈክሮች መካከል "ስንደመር እናምራለን፣ ኢትዮጵያዊነትን መጠየቅ አሸባሪነት አይደለም፣ በጨለማ የሚሄድ ህዝብ ብርሃን አየ፣ አማራነትን በፅኑ አለት ላይ እንገነባለን፣ ሞት ለገዳይ ቢሆንም መልሱ ግን ፈቅር ነው፣ እኛ ለዛሬው ነፃነት ብለን አልፈናል እናንተ ግን ተዋደዱ" የሚሉት ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም