ከተደመርን ወቅታዊ ፈተናዎችን በአንድነት መሻገር እንችላለን ... ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

134

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2012(ኢዜአ) ከተባበርንና ከተደመርን ወቅታዊ ፈተናዎችን በአንድነት መሻገር እንችላለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ገለጹ።

ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ለማሻገር ሁሉም በትጋት መስራት አለበት ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበረውን የለውጥ ጉዞ አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው "የለውጡን ጉዞ ሁለት ዓመት የምናከብረው በአንድ በኩል ስጋት፤ በሌላ በኩል የተስፋ ብርሃን ከፊታችን እያየን ነው" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በለውጥ ሂደት ያገኘቻቸውን ተስፋዎች ለማፍካት፣ ያጋጠሟትን ሳንካዎች ደግሞ ለማስተካከል እየጣረች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

አገሪቷ የገጠሟትን ሳንካዎች ለመፍታት እየጣረች ባለችበት በአሁኑ ወቅት መላው ዓለምን በጥቂት ወራት ውስጥ በቁጥጥሩ ስር ያዋለውና የማይታየው ጠላት የኮሮናቫይረስ በእኛም አገር አሻራውን እንዳሳረፈ ተናግረዋል።

"ነገ ምን ያህል ዜጎቻችንን እንደሚያጠቃ በእርግጠኝነት ባናውቅም ሁላችንም ተረባርበን በዝቅተኛ ጉዳት እንደምናስቆመው ግን ሙሉ እምነት አለኝ" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።

የለውጡ ጉዞ ሁለተኛ ዓመት ሲዘከር ምን ዓይነት ኢትዮጵያን እንገንባ የሚለውን በማሰብ መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።

ዶክተር ዐብይ ኢትዮጵያ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ስታልፍ ይሄ የመጀመሪያዋ እንዳልሆነና የመጨረሻዋም ላይሆን እንደሚችል አመልክተዋል።

"ከተባበርን፣ ከተደመርን በአንድነት ወቅታዊ ፈተናዎችን እንሻገራለን፤ የምንመኛትን፣ የምንጓጓላትን፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን እንገነባለን" ሲሉም ገልጸዋል።

ሁሉም ነገር ካለፈ በኋላ ወደቀደመው እንቅስቃሴያችን፣ ኑሯችንና ሕይወታችን እንመለሳለን ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

"ኢትዮጵያን ወደሚገባት ምዕራፍ እንደምናደርሳት አምናለሁ" ያሉት ዶክተር ዐብይ ለዚህም የሁሉም የሥራና ጸሎት ሕብረት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ይመለከተናል የሚሉ ሁሉ ለአገራቸው ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ እንዲሰጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የሁለት ዓመቱን የለውጥ ጉዞ አስመልክቶ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል ከዚህ በታች እንደሚከተለው ቀርቧል። ---------------------------------------------------------------------------------

ያልፋል አትጠራጠሩ!

ክቡራትና ክቡራን ኢትዮጵያውያን

ውድ የሀገሬ ሕዝቦች

የለውጡን ጉዞ ሁለተኛውን ዓመት የምናከብረው በአንድ በኩል ፈተናና ስጋት በሌላ በኩል የተስፋ ውጋጋን ከፊታችን እየታየን ነው፡፡ ሀገራችን ባለፉት ሁለት ዓመታት በለውጥ ሂደት ያገኘቻቸውን ተስፋዎች ለማፍካት፣ ያጋጠሟትን ሳንካዎች ደግሞ ለማስተካከል እየጣረች ባለችበት ወሳኝ ወቅት መላው ዓለምን በጥቂት ወራት ውስጥ በቁጥጥሩ ስር ያዋለው የማይታየው ጠላት የኮሮና ቫይረስ በእኛም አገር አሻራውን አሳርፏል፡፡ በእስካሁን ጉዞው 200 የሚጠጉ ሀገራትን ያዳረሰው ይህ ወረርሽኝ ወደ ሀገራችንም ገብቶ 29 ሰዎችን የቫይረሱ ተጠቂ አድርጓል፡፡ ነገ ምን ያህል ዜጎቻችንን እንደሚያጠቃ በእርግጠኝነት ባናውቅም ሁላችንም ተረባርበን በዝቅተኛ ጉዳት እንደምናስቆመው ግን ሙሉ እምነት አለን፡፡

ሀገራችን በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ስታልፍ ይኽ የመጀመሪያዋ አይደለም፤ የመጨረሻዋም ላይሆን ይችላል፡፡ በለውጡ ጉዞ የመጀመሪያው ምዕራፍ ወቅት በሶማሌ ክልል የተነሳውና በመሳሪያም፣ በጭካኔም እስካፍንጫው ታጥቆ የነበረው ሀይል በስልጣን ጥም ታውሮ አጎራባች ክልሎችን ሰላም ከማናጋት አንስቶ ክልሉን እስከመገንጠል የተለጠጠ ፍላጎት የነበረው ሲሆን፤ የለኮሰው እሳት የአፍሪካ ቀንድን እስከመረበሽ ሊደርስ ይችላል የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ መፈጠሩ አይካድም፡፡ ያም ሆኖ የለውጡ ዓላማ ኢትዮጵያን በፍትሕ የላቀች፣ በዴሞክራሲ የዳበረች፣ በሰብአዊ መብት ጥበቃ የተመሰገነች፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ በሰላምና በደኅንነት የተረጋጋች ሀገር ማድረግ ነበርና ከፈተናው ጎን ለጎን በተከናወኑ የሪፎርም ተግባራት ያ መጥፎ አጋጣሚ አልፎ እዚህ ደርሰናል፡፡

በተመሳሳይ የታጠቁ ኃይሎች በወለጋ እና በሌሎች የምእራብ ኦሮሚያ ክፍሎች ላይ የጥፋት በትራቸውን አሳርፈው ባንክ እየዘረፉ፣ ሰው እየገደሉ፣ ቤት እያቃጠሉ፣ መንገድ እየዘጉ፣ ትምህርት ቤት እየዘጉ ነዋሪውን እያማረሩ የነበረበት፤ ከገጠር ቀበሌዎች አልፎ እንደ ነቀምት፣ ጊምቢ እና ሻምቦ ባሉ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ መንግስታዊ መዋቅርን ለማፈራረስ የተንቀሳቀሰበት፤ የእለት ተእለት እንቅስቃሴዎች ያለወታደራዊ አጀብ የሚያስቸግሩበት ጊዜያትን አስተናግደናል፡፡ የለውጥ ጉዞው ይሄንንም መጥፎ ጊዜ አልፎ አሁን የሕዳሴ ግድብ ግንባታችንን እያጣደፍን፣ ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶቻችንን በማጠናቀቅ ተስፋችንን ሳይሆን ሪቫን እየቆረጥን ዛሬ ካለንበት ደርሰናል፡፡

በአንድ ቀን በአማራ ክልል ጠንካራ ጓዶቻችንን በግፍ አጥተን፤ በአዲስ አበባ ተወዳጅ የጦር መሪዎቻችን ተገድለው፤ ውጥረቱ ለድፍን ኢትዮጵያ ተርፎ የነበረበት ጊዜ አልፏል፡፡ እዚህና እዚያ እሳት በተለኮሰ ቁጥር ጥፋተኛው ይህና ያኛው ቡድን ነው እየተባለ፤ በየአካባቢው ሀያና ሰላሳ የታጠቀ ጦር ሠራዊት ያለ እስኪመስል ድረስ በየቦታውና በየጊዜው ሰዎች እየተገደሉ፤ አንድ ሰው አልበቃ ብሎ መንደር በሙሉ በእሳት ይጋይ የነበረበት፤ እልቂቱ በአንድ አካባቢ ሳይወሰን፣ ሁለትና ሦስት ክልሎችን ያነካካበት፤ ዜጎች ኢትዮጵያ ልትበታተን ትችላለች በሚል ስጋት ውስጥ እንዲቆዩ የሆነበት አስጨናቂ ጊዜን ተረማምደናል፡፡ ኃላፊነት በማይሰማቸው ሰዎች ንግግር ወንድም እህቶቻችንን የተቀጠፉበት፤ በትንሽ በትልቁ የህግ የበላይነት ያበቃለት፣ ኢትዮጵያም ያከተመላት እንዲመስል ተደጋጋሚ የጥፋት ርምጃዎች የተካሄዱበት ወቅት አልፎ ከሞላ ጎደል ወደ ሰላማችን ተመልሰናል፡፡

የለውጥ ጉዞው በየጊዜው የሚገጥሙትን ጋሬጣዎች ከመሻገር ባለፈ የተለያዩ የሪፎርም ተግባራትን ለማከናወን የተንቀሳቀሰበት ወሳኝ ወቅትም ነበር፡፡ በዚህም፣ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያችንን መሬት እንዲረግጥ ለማድረግ፤ ንግድን ለማሳለጥ የሚያስችል የዱይንግ ቢዝነስ ማሻሻያን በፍጥነት ለመተግበር፤ ከዓለም የንግድ ድርጅት ጋር ስኬታማ ድርድር ለማካሄድ፤ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የብድርና የርዳታ ተቋማት ጋር ኢኮኖሚውን ለመደገፍ የሚያስችሉ ውጤታማ ስምምነቶችን ለማድረግ ችለናል፡፡ በባንኮች ላይ የነበሩ የአሠራር ጫናዎችን ለማቃለል፣ ለሰብአዊ መብትና ለጋራ ተጠቃሚነት ዕንቅፋት የሆኑ ሕጎችና አሠራሮችን ለማስተካከል፤ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ሳይከሰቱ ለማምከን የሚያስችል አቅማችንን ለማደርጀት፤ ግጭቶችን የሚፈጥሩ ግለሰቦችን በሕግ ጥላ ሥር ለማዋል በሙሉ አቅማችን ተንቀሳቅሰናል፡፡ ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ እያመሩ የነበሩ በዩኒቨርሲቲዎችን ወደ መልካም መማር ማስተማር ሂደት ማምራት የሚችሉበት አጋጣሚ ተፈጥሮ፣ ስለ ምርጫ፣ ስለ ሀገራችን ብልጽግና እና ስለ ወደፊቷ ጠንካራ ኢትዮጵያ ማሰብ በጀመርንበት ወቅት እነሆ ሌላ ጋሬጣ ከፊታችን ቆሟል፡፡ ምንም እንኳ ፈተናው የመጣው ለመላው አለም ቢሆንም ከፊታችን የተደቀነውን ችግር ለመጋፈጥ እንደ ቀደሙት ጊዜያት ጉልበታችን ላፍታ ሸብረክ እንደማይል ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡ ሁሌም እንደምናደርገው ሕዝባችንን አስተባብረንና ዐቅማችንን ደምረን በድል ከተሻገርነው በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ጀመርናቸው ሀገራዊ ሪፎርሞች ፊታችንን እንደምናዞር ጥርጥር የለኝም፡፡

ሀገራዊ ለውጥን በጽኑ መሰረት ላይ የመትከል ትግላችንን ጊዜያዊ ፈተና አይገታውም፡፡ አሁን በዓለም ደረጃ የተከሠተውን ዓይነት ፈተና ወደፊትም ይገጥመን ይሆናል፡፡ “ስለ ነገ በትክክል ለመተንበይ የተሻለው ዘዴ ዛሬ ላይ ሆኖ የወደፊቱን መፍጠር ነው” እንዲሉ ለሚገጥሙን ፈተናዎች የዝግጁነት አቅማችንን እያሳደግን እንቀጥላለን፡፡ ኢትዮጵያን ከፈተናዎች በላይ እንድትሆን አድርገን ለመገንባት የሁላችንም ርብርብ ይጠይቃል፡፡ እስካሁን ባለው ጉዟችን የሀገራችንን ኢኮኖሚ፣ ተቋማቶቿን፣ የፍትሕ ሥርዓቷን፣ ማኅበራዊ ደኅንነቷን፣ የሕግ አስከባሪ አካላትን፣ የጤናና የትምህርት ሥርዓቷን በማጠናከር ፈተናዎችን መቋቋም በሚችሉበት ደረጃ ለማደራጀት ጠንካራ የዐቅም መሠረት መጣል ጀምረናል፡፡ ዐቅም ግንባታ ስትራቴጂያዊ ዕይታን የሚጠይቅ፣ ተከታታይ ስራን የሚፈልግ እና ፈጽሞ የማያቋርጥ ረጅም ሂደት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይኽም ደግሞ እንደኛ ድሀ በሆኑ ሀገራት ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ግንባር ቀደም የሆኑትን ጭምር የሚመለከት መሆኑ የሰሞኑ ዓለም አቀፋዊ ፈተና ምስክር ነው፡፡

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት እንኳን እኛን ጠንካራ የጤና መሠረተ-ልማት የገነቡትን ምዕራብያውያን ምን ያህል እያስጨነቀ እንዳለ ሁላችንም እንገነዘባለን፡፡ በብዙ ሀገራት ትምህርት ቤቶች ከተዘጉ ሰነባብተዋል፡፡ በድንበሮች አካባቢ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ ነው፤ የንግድና ስራ እንቅስቃሴዎችም በከፊል ተቋርጠዋል፡፡

የዶላር ግኝት አለኝታችን የሆነው እና ከሀገራችን አልፎ የአፍሪካችን የኩራት ምንጭ የሆነው አየር መንገዳችን እንቅስቃሴው በከፊል ተገቷል፡፡ የአበባ ኤክስፖርት ንግዳችን የሚያንሰራራበት ጊዜ በውል ባልታወቀ አጣብቂኝ ውስጥ ተቀርቅሯል፡፡ በኤክስፖርት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በፋይናንስ ዘርፎቻችን ላይ የተደቀነው ተግዳሮት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

ምንም እንኳ እየገጠመን ያለው ችግር ከዚህ በፊት እንዳየናቸው አደጋዎች የማያልፍ ቢመስልም ማለፉ ግን አይቀርም፡፡ ስለተመኘን ሳይሆን በትብብር ስለምንሰራ ይህ ጊዜ ያልፋል፡፡ ከወዲሁ እውቀታቸውን፣ ሀብታቸውን፣ ጊዜና ጉልበታቸውን በመስጠት የትብብር አቅማቸው ምን ያህል እንደሆነ እያሳዩን ያሉ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ለዚህ ምስክር ናቸው፡፡

ውድ የሀገሬ ህዝቦች!

የለውጡን ጉዞ ሁለተኛ ዓመት ስንዘክር ምን ዓይነት ኢትዮጵያ እንገንባ የሚለውን እያሰብን መሆን አለበት፡፡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የጠነከረ፤ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ያረጋገጠችና ለዜጎቿ ምቹ የሆነች፤ለኢንቨስትመንት ተመራጭ፣ የምሥራቅ አፍሪካ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ማዕከል የማድረግ ርዕይ በውስጣችን ልንሰንቅ ይገባል፡፡ ሰላሟና ደኅንነቷ የተረጋገጠ፤ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጋር ያገናዘበች፤ በአፍሪካ ለቱሪስቶች ተመራጭ የሆኑ መዳረሻዎች ያሏት፤ መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብቶቿን በሚገባ ማልማት የምትችል ሀገር መገንባትን ታሳቢ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

ይህችን ብሩህ ተስፋ የሰነቀች ሀገር ተሳክቶላት ለማየት ካለፉት ስሕተቶቻችን እየተማርን፣ ያሉንን ወረቶች ይዘን፤ ከሚያራርቁን ይልቅ ለሚያቀራርቡን ነገሮች ትኩረት እየሰጠን፤ ከትናንት ይልቅ ነገ ላይ እያተኮርን መጓዝ አለብን፡፡ ዓለም ከነገ ጋር ለመወዳደር እየሮጠ ነው፡፡ተወዳድረን ማሸነፍ ከፈለግን መሮጥ ቀርቶ መራመድ፣ መራመድ ቀርቶ መቆም፣ መቆም ቀርቶ መተኛት ለእኛ ፍጹም አያዋጣንም፡፡ ያለችንን ጥቂት ጉልበት ይዘን ሽምጥ ለመፈትለክ መፍጨርጨር ነው ምርጫችን፡፡ ሙሉ ትኩረታችንን ታላቁ ሀገራዊ ዓላማ ላይ አድርገን ከተጓዝን ከወጀቡ ባሻገር በስኬት እንሸለማለን፡፡

በመጨረሻም ቀጣዩ የለውጥ ዘመን ካሳለፍናቸው ሁለት የለውጥ ምዕራፎች የተሻለ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሀገራችንን ወደሚገባት ምእራፍ እንደምናደርሳት አምናለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ የሁላችን የሥራና ጸሎት ሕብረት ያስፈልጋታል፡፡ ከቀበሌ እስከ ፌደራል ባሉ የተለያዩ የሀላፊነት እርከኖች፤ ከአርሶና አርብቶ አደር ማህበሮች እስከ ንግድና ኢንቨስትመንት ማዕከላት፤ በተለያየ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ሞያተኞች፤ ልሂቃን፤ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት፤ በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፤ በየግንባሩ የተሰለፋችሁ የሠራዊት አባላት፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ይመለከተናል የምትሉ ሁሉ ለሀገራችን ጉልበታችሁን ሳትሰስቱ እንድትሰጧት በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

ተባበርን፣ ተደመርን፣ በአንድነት ወቅታዊ ፈተናችንን እንሻገራለን፤ የምንመኛትን፣ የምንጓጓላትን፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን እንገነባለን፡፡ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች፣ መስሪያ ቤቶችና ድንበሮች ይከፈታሉ፤ የተቀዛቀዘ ኢኮኖሚያችን ዳግም ያንሰራራል፡፡ ላልተወሰነ ጊዜ የምናደርገው መራራቅ በመቀራረብ ይተካል፡፡ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ወደነበሩበት ይመለሳሉ፡፡ ሞትም በሕይወት ይሸነፋል፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ

መጋቢት 24/ 2012 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም