በደሴና ጎንደር በሺሻ፣ ጫትና ፑል ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

71

ደሴ /ጎንደር መጋቢት 24/2012 (ኢዜአ) በደሴና ጎንደር ከተሞች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሺሻ፣ ጫትና ፑል ቤቶች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ።

በተጨማሪም በጎንደር ከተማ ሶስት ህገ ወጥ ሽጉጦች በቁጥጥር ስር መዋሉ ተመልክቷል፡፡

በደሴ ከተማ  አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ አስወጋጅ ግብረ ኃይል  ሰብሳቢ ዋና ኢንስፔክተር ሃሰን መሃመድ እንዳሉት የጫት፣ የሽሻና የፑል ቤቶቹ ወጣቶች ተሰባስበው በጋራ የሚጠቀሙባቸው ናቸው።

ግብረ ኃይሉም ለበሽታው ስርጭት ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን በማጥናት 97 የጫት እንዲሁም 110 የፑልና ሽሻ ቤቶችን በመዝጋት እርምጃ ወስዷል።

በከተማዋ የበሽታውን ስርጭት ለመግታተም የትራንስፖርት አገልግሎትና ዋና ዋና የገበያ ቦታዎች እንዲዘጉ ማድረጉን ጠቁመው "በቀጣይም እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎች እርምጃዎች ይወሰዳሉ "ብለዋል።

በተያያዘ ዜና የጎንደር  ከተማ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር እየሩስ አስማረ እንደገለጹት ከ4 መቶሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው የሺሻ እቃዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።

ሶስት ህገ ወጥ ሽጉጦች ከዘጠኝ ጥይቶች ጋርም በቁጥጥር ስር መወሉንም አመልክተዋል።

የሺሻ እቃዎቹና ሽጉጦቹ የተገኘበት በከተማው ቀበሌ አስር ነዋሪ የሆነውን ግለሰብ በተጠርጣሪነት  ተይዞ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑን ዋና ኢንስፔክተር እየሩስ ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ ህገ ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ግለሰቦችን በማጋለጥ የኮሮና በሽታን በመከላከል የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክት ተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም