የጤና ባለሙያዎች ስለኮሮና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጡ

58

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል የጤና ባለሙያዎች ከጤና ሚኒስቴር ና ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ ጎዳናዎች በመዘዋወር የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጡ።

የጤና ባለሙያዎቹ በሙያቸው ህሙማንን ለመንከባከብ እየሰሩ በመሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ባለሙያዎቹ የሚሰጡትን የጥንቃቄ መመሪያዎች ገቢራዊ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

እጅን መታጠብ፣ አለጨባበጥ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን መግታት፣ የህመም ምልክቶች ከተስተዋሉ ሌሎችን ላለመጉዳት መጠንቀቅና ወደ ህክምና መሄድ የሚሉትን የጥንቃቄ መልዕክቶች አስተላልፈዋል።

ባለሙያዎቹ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለህሙማን ተገቢውን እንክብካቤና እርዳታ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጤና ባለሙያዎቹ መነሻቸውን ከጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በማድረግ ሰው ወደሚበዛባቸው አካባቢዎች በመዘዋወር የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም