በአማራ ክልል 5 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተሰማሩ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል 5 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተሰማሩ
ባህርዳር መጋቢት 24/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያግዙ አምስት ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መሰማራታቸውን የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አባይነህ መላኩ ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሮና በሽታ ስርጭትን ለመከላከል ወጣቶችን በማደራጀት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል።
በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ ወደ ስራ ከመግባታቸው በፊት በባለሙያዎች የተደገፈ በቂ ስልጠና ተሰጥቶአቸዋል ።
በጎ ፈቃደኞቹ በባህርዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ እንጂባራና ደብረ ብርሃን ከተሞችን ጨምሮ በሌሎች
ከተሞች መሰማራታቸውን አመልክተዋል።
ለወጣቶቹ በየከተሞቹ ያሉ የሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ተቋማትና የጤና ባለሙያዎች አማካኝነት ተገቢውን ድጋፍና እገዛ እያደረጉላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም በጎ ፈቃደኞቹ ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ድንኳን በመትከል እጅ የማስታጠብ፣ አካላዊ ጥግግትን እንዳይኖርና የእጅ በእጅ ሰላምታ ለማስቀረት የግንዛቤ መፍጠር ስራ እያከናወኑ ይገኛል።
ድጋፍ ለሚያሰፈልጋቸው ሰዎች ጥሬ ገንዘብም ሆነ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስና የእለት ምግብ የማሰባሰብ ስራዎች እያከናወኑ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
ወጣቶቹ መለዮ ለብሰው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን እየሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ጉዳዩ እየባሰ የሚሄድ ከሆነ ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ የምግብም ሆነ ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ይደረጋል።
ህብረተሰቡ በጎ አድራጊ ወጣቶች የሚሰጡትን አገልግሎትና ምክር ተግባራዊ በማድረግ እራሱን ከኮሮና ቫይረስ ሊከላከል እንደሚገባም ምክትል ቢሮ ሃላፊው አሳስበዋል።
የክልሉ የበጎ አድራጊ ወጣቶች አስተባባሪ አቶ ጋኛው ተቀባ በበኩሉ ህብረተሰቡ በየጊዜው የሚሰጡ መመሪያዎችን ፈጥኖ እንዲተገብር በማድረግ ከበሽታው ለመጠበቅ እገዛ እየተደረገ ነው።
በሽታውን ከወዲሁ ለመከላከል የመንግስትም ሆነ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን ምክረ ሃሳቦች ህብረተሰቡ ተቀብሎ እንዲተገብር በተግባር የታገዘ የበጎ ፈቃድ ስራ እየተከናወነ ነው።
ወደ ስራ ከመገባቱ በፊት ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሶ አሁን ላይ በየከተሞቹ የበጎ ፈቃድፍ አገልግሎቱ በተናበበ አግባብ እየተሰራ መሆኑን ተናግሯል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመሰማራት 40 ሺህ ወጣት መለየቱን አመልክቶ በቀጣይ ችግሩ እየተባባሰ ከመጣ ሁሉንም በማሰልጠን ወደ ስራ ለማሰማራት መታሰቡን ገልጿል።
የበሽታውን አሳሳቢነት በመረዳት ከጤና ባለሙያዎች በተገኘው ምክረ ሃሳብ መሰረት በከፍተኛ የሃላፊነት መንፈስ ወደ ስራ መሰማራታቸውን የገለፀው ደግሞ የምስራቅ ጎጃም ዞን በጎ አድራጊ ወጣቶች አስተባባሪ ወጣት ቢሻው ሞላ ነው።
እንደ ምስራቅ ጎጃም ዞን ከ2 ሺህ 800 በላይ ወጣቶች በዞኑ በሚገኙ 17 ወረዳዎች ተሰማርተው የበጎ አድራጎት ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ ብሏል ።
በአማራ ክልል ከኮሮና በሽታ መከሰት ጋር በተያያዘ በባህር ዳር፣ እንጂባራ፣ አዲስ ቅዳምና ቲሊሊ ከተሞች ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉ ይታወሳል።