“ጥንቃቄ ባደረግን ቁጥር ራሳችንንም፣ ቤተሰቦቻችንንም፣ አገራችንንም እየጠበቅን ነው!” ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

103

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2012(ኢዜአ) የከተማ ልማት ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ዛሬ ማምሻውን በአዲስ አበባ  በመገናኛና በሾላ ገበያ አካባቢዎች በመዘዋወር ህብረተሰቡ  ከኮረና ወረርሽኝ ራሱን እንዲጠብቅ ሲያስተምሩና መልዕክት ሲያስተላልፉ አምሽተዋል፡፡

 ሚኒስትሯ  በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ህብረተሰቡ ከጤና ባለሙያዎችና ከመንግስት የሚሰጡ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በመቀበል በትኩረት መተግበር አንዳለበት አሳስበዋል፡፡

‹‹ ውድ ወገኖቼ ! ሁላችንም እንደአንድ የምናስብበት  ጊዜ ላይ ነን!  የኮረና ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰራጭ ወረርሽኝ ቢሆንም መከላከል የምንችልባቸውም መንገዶች በእጃችን ናቸው!  ጥንቃቄ ባደረግን ቁጥር ራሳችንንም፣ ቤተሰቦቻችንንም፣ አገራችንንም እየጠበቅን ነው! ›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹ ህብረተሰቡ  በተወሰነ መልኩ የጥንቃቄ መልዕክቶችን እየተገበረ ቢሆንም አሁንም ቸልተኝነት ይስተዋላል›› ያሉት ሚኒስትሯ ‹‹ እባካችሁ በማንኛውም ቦታዎች ላይ  ስንገበያይ፣  በአገልግሎት ቦታዎች ስንገኝ፣ ትራንስፖርት በምንጠቀምባቸው  አካባቢዎች ርቀታችንን እንጠብቅ! የግልና የአካባቢ ንፅህናችንን  በመጠበቅ  ከወረርሽኙ ነፃ የሆኑ ከተሞች እንዲኖሩን በጋራ እንስራ!›› ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በወቅቱም በመገናኛና በሾላ ገባያ አካባቢ  በርካታ የህብረተሰቡ ክፍሎች ርቀትን ያለመጠበቅና ተፋፍጎ የመገበያየት ሁኔታዎች ይስተዋሉ የነበረ ሲሆን ሚኒስትሯም ‹‹ እባካችሁ ቸልተኝነት ይብቃ! እንንቃ! ርቀታችንን በመጠበቅ! ቤተሰቦቻችንን እንታደግ ›› ሲሉ ተማፅነዋል፡፡