ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው

62

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2012  (ኢዜአ) ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል ወደ ማዕከላት ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

በሚኒስቴሩ የማህበራዊ ደህንነት ልማት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ፈለቀ ጀምበር ለኢዜአ እንደገለጹት ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎች ለኮሮናቫይረስ ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ለሚሰሩ ስራዎች የሶስት ወር እቅድ ተዘጋጅቷል።

ዜጎቹን ባሉበት ተደራሽ ማድረግ የማይቻል በመሆኑና የአቅርቦት ችግርም ሊኖር ስለሚችል ካሉበት ተነስተው ወደ ማዕከል እንዲገቡ አቅጣጫ መቀመጡን ነው ያነሱት፡፡

በዚሁ መሰረት ዜጎቹን የማንሳትና ወደ ማዕከላት የማስገባት ስራ ለማከናወን የቅድመ ዝግጅት  ስራዎች እየተከናወኑ ነው ያሉተት ዳይሬክተሩ፣ ሰዎች በጎዳና ላይ ሆነው በሚኖሩበት ሁኔታ በሽታውን መከላከል አዳጋች ስለሚሆን ነዋሪዎቹ ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ ወደተዘጋጀላቸው ማዕከል እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡

በየከተሞቹ በተዘጋጁት ማዕከሎች በሚኖራቸው ቆይታም  ምግብን ጨምሮ የሚስፈልጓቸው ነገሮች እንደሚሟሉና ስራውን ከአገለግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ደረጃ በጎዳና ላይ ኑሯቸውን ያደረጉ ወገኖችን ለማንሳት የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁንም አመልክተዋል።በከተማዋ የሚገኙትን 50 ሺህ ገደማ የጎዳና ላይ ነዋሪዎች በተወሰኑ ቀናት እንደሚነሱም በመግለጽ፡፡

ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሁሉም ከተሞች በተለይም በዋናዋና ትላልቅ ከተሞች ያሉትን ለማሰባሰብ መታቀዱንም አመልክተዋል።

መንግስትና የልማት አጋሮች በጋራ እየሰሩ እንደሆነ አንስተው  ማህበረሰቡም በሚጸድቀው እቅድ መሰረት አጋር እነቱን እንዲያሳይ ጠይቀዋል፡፡

የኮሮናቫይረስ ስለመጣ ብቻ ሳይሆን በጎዳና ላይ የሚኖሩ ወገኖችን በዘላቂነት የማቋቋምና የመደገፍ ስራ ሁልጊዜም መሰራት ያለበት ጉዳይ እንደሆነ የያስረዱት አቶ ፈለቀ  ሚኒስቴሩ በ11 ከተሞች ተግባራዊ እየሆነ በሚገኘው የከተማ የልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃግብር በጎዳና ላይ ኑሯቸውን ያደረጉ ዜጎችን ተጠቃሚ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በጎዳና ላይ ኑሯቸውን ያደረጉ ዜጎችን የማቋቋም ስራ የአንድ ተቋም ድርሻ ባለመሆኑ ሁሉም አካል የበኩሉን ሃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት በ11 ዋና ዋና ከተሞች ላይ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት 88 ሺህ 690 ሰዎች ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ማድረጋቸውን ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም