ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከግዴታ ለይቶ ማቆያ በሚወጡ ሰዎች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ... ዶክተር ሊያ ታደሰ

236

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2012( ኢዜአ) ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከግዴታ ለይቶ ማቆያ በሚወጡ ሰዎች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

ለኮሮናቫይረስ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ከአገር ውስጥና ከውጭ ተቋማት በማስገባት ያለውን አገልግሎት ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ሚኒስትሯ አስታወቀዋል።

የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከል ከመጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ጀምሮ ማንኛውም ከውጭ አገር የሚመጣ መንገደኛ በተመረጡ ሆቴሎች ውስጥ በራሱ ወጪ ለ14 ቀናት ተለይቶ እንዲቆዩ የተወሰነ መሆኑ ይታወቃል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ከውጭ አገሮች የሚገቡ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንና ይሄን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለይቶ ማቆያዎችን የማስፋት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ሆኖም የተወሰነውን ውሳኔ በመጣስ ከግዴታ ለይቶ ማቆያ እየወጡ በመሆኑ ሚኒስቴሩ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑንና ይሄም ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ከሕብረተሰቡ የሚመጡ ጥቆማዎችን በመቀበልና በማጣራት ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አስረድተዋል።

የኮሮናቫይረስ ለመከላከል እንደ አገርና ዓለም አቀፍ ትልቁ ተግዳሮት የሆነው የግብአት አቅርቦት እጥረት መሆኑን ጠቅሰው ይሄ ሁኔታ እንዲሻሻልም ከአገር ውስጥና ከውጭ ተቋማት ግብአቶችን የማሟላት ስራ መቀጠሉን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ አካላዊ ርቀትና የግል ንጽህናውን በመጠበቅ እንዲሁም ቫይረሱን አስመልክቶ የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ተግባራዊ በማድረግ  ስርጭቱ እንዳይስፋፋ ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ዶክተር ሊያ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 29 መድረሱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም