በአምስት የስደተኞች መጠለያ ጣብያዎች የኮሮና ቫይረስ የመከላከል ስራ እየተከናወነ ነው

55

አሶሳ ኢዜአ መጋቢት 23 ቀን 2012 ዓም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአምስት የስደተኞች መጠለያ ጣብያዎች የሚገኙ ከ60 ሺህ በላይ ስደተኞች ከኮሮና ቫይረስ የመከላከል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተገለጠ።
በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አስተዳደር ጉዳይ የአሶሳ ማስተባበርያ ሃላፊ አቶ አምደወርቅ የኋላወርቅ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ ሸርቆሌ ፣ ቶንጎ ፣ ባምባ ፣ ፆሬና ጉሬ የሚባሉ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ።

በጣቢያዎቹ ቁሳቁሶችን ማቅረብ ፣ ማህበራዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ የማስተማርና ሌሎች የመከላከል ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች የሚከናወኑት በካምፖች ከሚሰሩ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ፣ ከአካባቢው መንግስታዊ አካላትና ከስደተኞች ጋር በመተባበር ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ለህክምና ካልሆነ በስተቀር ከካምፑ የሚወጣ ስደተኛ የለም ያሉት ሃላፊው በካምፑ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ፣ መዝናኛዎችና የማህበራዊ አገልግሎቶች በሙሉ መቆማቸውን ገልፀዋል ።

በቅርቡ የስደተኞችን የሰውነት ሙቀት ምርመራ ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።

የክልሉ ርእሰ መሰተዳድር አቶ አሸድሊ ሐሰን በበኩላቸው ግብረ ሃይሉ በክልሉ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች  የቫይረሱ ስርጭት እንዳይስፋፋ የመከላከል ስራ እየተከናወነ ነው ።

 በቅርቡ ክልሉ ከሱዳን ጋር በሚዋሰንባቸው ድንበሮች በኩል ወደ ክልሉ ለመግባት የሞከሩ ህገ ወጥ ግለሰቦች ወደ መጡበት እንዲመለሱ መደረጉን ገልፀዋል።

 በክልሉ በሚገኙ አምስት የሰደተኛ ጣቢያዎች ከ60 ሺህ በላይ የተለያዩ አፍሪካ ሀገራት ስደተኞች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም