የአየር ንብረት ለውጥ የዘማሪ ወፎችን ህይወት አደጋ ላይ ጥሏል

99

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2012  (ኢዜአ) የስፔን ተመራማሪዎች ለ20 ዓመታት ባደረጉት ጥናት  የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው ሙቀት ትናንሽ  ዘማሪ ወፎች ተመናምነዋል፡፡

ተመራማሪዎቹ እንዳሉት እየጨመረ የመጣውን የአለም ሙቀት ተከትሎ የምግብና ውሀ እጥረት  ዘማሪ ወፎቹ  እንዲሰደዱና ቁጥራቸው እንዲመናመን አድርጓል፡፡

እነዚህ ወፎች መገኛቸው በአብዛኛው  በአውሮፓና ኤዥያ እንዲሁም ደቡብ እንግሊዝ ሲሆን ባለፉት ሐምሳ ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው ችግር 90 በመቶ ዝርያቸው እንደቀነሰ ተገልጿል፡፡

በጥናቱ መሰረት ዘማሪ ወፎቹ ተፈጥሮ በሰጠቻቸው ጸጋ ከአንድ ሺ በላይ የድምጽ አይነቶችን የሚያወጡ ሲሆን 340 ገደማ ህብረ ዝማሬ ደግሞ ይፈጥራሉ፡፡

በክረምት ወራት ከሰሀራ በረሀ በታች ወዳሉ አገራት በመሰደድ ውሀና ምግብ የሚያገኙት አእዋፋቱ የአየር ንብረት ለውጡ ባስከተለው ችግር  ረጅም ጉዞ ማድረግ እንዳልቻሉ ተጠቅሷል፡፡

ይህም በክንፎቻቸው ማነስና በድርቅ ምክንያት የተሟላ የመራቢያ ጊዜ ባለማግኘታቸው ሲሆን አእዋፋቱ ረጅም ርቀት ተጉዘው ለመመለስ የሚሆን የሰውነት አቅም የላቸውም ነው የተባለው፡፡   

ጥናቱ በስፔንና በቀጠናዋ  ይካሄድ እንጂ የአየር ንብረት ለውጡ በሌሎች አካባቢ ባሉ የአእዋፍት ዝርያዎች ላይም  እየደረሰ ያለው ተጽህኖ ማሳያ ነው ሲሉ ተመራማሪዎቹ መናገራቸውን ያስነበበው ቢቢሲ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም