በአውስትራሊያ ሜልቦርን የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ

68
አዲስ አበባ ሰኔ 24/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ እያከናወኗቸው ያሉ የለውጥ እርምጃዎችን በመደገፍ ዛሬ በአውስትራሊያ ሜልቦርን ከተማ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ። ዶክተር አብይ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸው ጸድቆ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ መንግስት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በተለያዩ መስኮች የማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና መንግስታቸው እያካሄዱት ያሉትን የለውጥ እርምጃዎች በመደገፍ በአውስትራሊያ ሜልቦርን ከተማ የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ መካሄዱን በአገሪቷ የሚገኙ የዜና ወኪሎች ለኢዜአ ገልጸዋል። በድጋፍ ሰልፉ ላይ የነበሩ ተሳታፊዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን የሰላም፣ የፍቅር፣ የይቅርታና የአንድነት በአጠቃላይ የመደመር መልዕክትና ጥያቄ እንደሚደግፉ ነው የተናገሩት። ሰልፈኞቹ አንድነት፣ ሰላምና ፍቅርን የሚያሳዩ መፈክሮችን ይዘው  የወጡ ሲሆን "ኑ በፍቅር፣ በይቅርታና በፍትህ እንደመር" የሚለው መፈክር በዋነኛነት ይጠቀሳል። እንደ ሰልፈኞቹ ገለጻ "ዛሬ የድጋፍ ሰልፍ የወጣነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ እየወሰዷቸው ያሉ እርምጃዎች ያለ ህዝብ ድጋፍ ቀጣይነት ስለማይኖረው እኛም የበኩላችንን ድጋፍ ለመስጠት ነው" ብለዋል። የተለያዩ የእምነት አባቶች በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙ ሲሆን ህዝቡ የቀረበውን ጥሪ ተቀብሎ ለአገሩ አንድነት፣ ሰላምና ፍቅር እንዲሰራ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። የሰልፉ ተሳታፊዎች በአውስትራሊያ የተለያዩ ግዛት የተውጣጡ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው የዜና ምንጮቹ ገልጸዋል። ከአራት ቀናት በፊት በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እየወሰዱ ያሉ የለውጥ እርምጃዎችን በመደገፍ የድጋፍ ሰልፍ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም