ቦርዱ በጊዜ ሰሌዳው መሰረት ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል ገለጸ

217

መጋቢት 22፣ 2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫውን ማካሄድ እንደማይቻል አስታወቀ።

ቦርዱ ባወጣው መግለጫ ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ በመሰረዝ በሰሌዳው መሰረት መከናወን ያለባቸው ተግባራት ለጊዜው እንዲቆሙ መወሰኑን ጠቁሟል።

በዚህ ዓመት የሚካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ ለማስፈፀም የቅድመ ምርጫ ዝግጅት ስራዎች ሲከናወኑ የነበረ ሲሆን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ መሆኑም ይታወሳል።

ይሁንና በዚህና በቀጣዩ ወር መጠናቀቅ የነበረባቸው ስራዎች በወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መጓተት ማሳየታቸውን አስታውቋል።

የመራጮች ምዝገባ፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላ፣ ስልጠናና ስምሪት፣ የመራጮች ትምህርት፣ ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ስርጭት የመሳሰሉት ከተግባራቱ መካከል ይገኙበታል።

ወረርሽኙን ለመግታት መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ በመሆኑ፤ በክልል መንግስታትም የተለያዩ ገደቦች መቀመጣቸውና ለቦርዱ ድጋፍ የሚያደርጉ አጋር ድርጅቶች አብዛኞቹ ሰራተኞቻቸው ከቤት ሆነው እንዲሰሩ፤ ሌሎቹም ጥቂቶቹ ብቻ እንዲሰሩ በማድረጋቸውና በሌሎችም በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጿል።

በጉዳዩ ዙሪያ ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተደረገው ውይይት አብዛኞቹ የችግሩን ግዝፈት እና በምርጫ ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ ተገንዝበው ቦርዱ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ተመካክሮ አማራጭ የአፈጻጸም ዕቅድ ሊኖረው እንደሚገባ መምከራቸውንም አስታውቋል።

በውሳኔው መሰረት የሚሆነው የዳሰሳ ጥናት በአማካሪ ባለሙያዎቹ ተሰርቶ እንዲቀርብለት ማድረጉንም ነው ቦርዱ በመግለጫው ያመለከተው።

ቦርዱ የወረርሽኙ ሥጋት ተወግዶ ሁኔታዎች ሲመቻቹ እንደገና ግምገማ በማድረግ አዲስ የምርጫ ዘመቻ እቅድና የግዜ ሰሌዳ በማውጣት እንቅስቃሴ እንደሚያስጀምርም ጠቁሟል።

ቦርዱ ባደረጋቸው ምክክሮችና የዳሰሳ ጥናት ላይ በግልጽ የተለዩ፣ በኮቪድ 19 የማይስተጓጎሉ፣ የቦርዱን የምርጫ አፈጻጸም ዝግጁነት የሚጨምሩ፣ ሁኔታው ተቀይሮ ተቋሙ ወደ መደበኛ ተግባሩ ሲመለስ በተገቢው ሁኔታ ምርጫን ለማስፈጸም የሚያሥችል ሁኔታን የሚፈጥሩ ተግባራትን እያከናወነ መቆየት እንዳለበትም ወስኗል።

በህገ መንግስቱ በተቀመጠው መሰረት በስራ ላይ የሚገኘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስልጣን ጊዜው ከሚያበቃበት አንድ ወር አስቀድሞ ቦርዱ አጠቃላይ ምርጫ ማድረግ የማይችል መሆኑን ተገንዝቦ፣ ከዚህ አንጻር የሚሰጠው ውሳኔ ቢኖር ለመነሻነት ያገለግለው ዘንድ ውሳኔውና ቦርዱ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት ሰነድ ለህዝብ ተወካዮች እንዲተላለፍለት መወሰኑንም በመግለጫወ አስታውቋል።