ፓርቲዎች ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በጋራ እንዲቆሙ ተጠየቀ

157

አዲስ አበባ መጋቢት 22/2012(ኢዜአ) ፓርቲዎች የፖለቲካ ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በጋራ እንዲቆሙ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ። 

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በወቅታዊ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትና መከላከልን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም እንዳሉት ፓርቲዎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ከፖለቲካዊ አጀንዳቸው ሊያስቀድሙት ይገባል።

“ህዝብ ከሌለ የሚመሩት ህዝብና አገር ስለማይኖር የኮሮና ቫይረስል ለመከላከል ሕብረተሰቡ ማድረግ በሚገባው ቅድመ ጥንቃቄ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ መስራት ይኖርባቸዋል” ብለዋል።

ኢትዮጵያ አሁን የገጠማት ፈተና ፓርቲዎች ለህዝብ ያላቸውን ወገንተኝነት በቁርጠኝነት የሚያሳዩበት ጊዜ እንደሆነም አቶ ሙሳ ተናግረዋል።

ፓርቲዎች እርስ በርስ የፖለቲካ ልዩነት ቢኖራቸውም ይህን ልዩነት ወደጎን በመተው በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በጋራ እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ ሰብሳቢው ገለጻ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሕብረተሰቡን ከማስገንዘብ ባለፈ በቻሉት አቅም ለኮቪድ-19 ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ እገዛ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

መንግስትም የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቁመው የቫይረሱ ስርጭት ወደ አርሶና አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ እንዳይዛመት ትኩረት እንዲደረግባት አስገንዝበዋል።

“ከጎረቤት አገሮች ሊመጣ የሚችለውን ተጨማሪ አደጋ ለመቀነስ መንግስት በድንበሮች አካባቢ ፍተሻውን ማጠናከርና የለይቶ ማቆያ ማዕከላትን መገንባት ይኖርበታል” ብለዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ በበኩላቸው “የምክር ቤቱ አባል የሆነው ብልጽግና ፓርቲ በሰዎች የጋራ መሰብሰብ ላይ የሚያሳየው ቸልተኝነት መታረም አለበት” በማለት ተናግረዋል።

ፓርቲው በአፋር፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም በሌሎች ክልሎች በመቶዎች ለሚቆጠሩ ለዝቅተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና እየሰጠ ነው ሲሉም ወቅሰዋል።

የኮሮናቫይረስ ዓለምን እያስጨነቀ ባለበት በአሁኑ ወቅት ብልጽግና ፓርቲ እየሰጠ ያለው የአመራር ስልጠና ተገቢነት የሌለው በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲያቆም ሲሉም ጠይቀዋል።

ይሁንና ስለ ጉዳዩ ኢዜአ የጠየቃቸው የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወሉ አብዲ በአሁኑ ወቅት በብልጽግና ፓርቲ እየተሰጠ ያለ ምንም አይነት ስልጠና የለም ብለዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ፓርቲው ቀደም ሲል ለከፍተኛና መካከለኛ የፓርቲና የመንግስት የስራ አመራሮች ከለውጡ ጋር ተያይዞ መልካም አስተዳደርን ጨምሮ ህዝቡ ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ ነበር።

በዚህ መሐል የኮሮና ወረርሽኝ ከፍተኛ ስጋት በመደቀኑ ቀጥሎ ይካሄድ የነበረውን ስልጠና መልክ በመቀየር ወርሽኙን ለመከላከል የተዋቀረው ብሔራዊ ኮሚቴ ባስቀመጠው መሰረት ርቀትን ጠብቆ የተወሰኑ ሰዎች ባሉበት ስለ ወረርሽኙ መረጃ መለዋወጫ መድረክ መደረጉን አስታውሰዋል።

ይህ የተደረገውም አመራሩ ስለ ወረርሽኙ ግንዛቤ ኖሮት ራሱን እና ህብረተሰቡን እንዲጠብቅ፤ መረጃ በማይደርስባቸው አካባቢዎች ጭምር በመውረድም ያለውን ክፍተት እንዲሞላ በማሰብ ነው ብለዋል።

በመሆኑም አመራሮቹ ያገኙትን ግንዛቤ ወደ ህብረተሰቡ ለማድረስ ዘመቻ መጀመራቸውን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት ብልጽግና ፓርቲ እየሰጠ ያለው ስልጠና የለም ሲሉ ተናግረዋል።