በምዕራብ ኦሮሚያ ተቋርጦ የነበረው የቴሌኮም አገልግሎት ከዛሬ ጀምሮ ዳግም እንዲጀመር ተወሰነ

86

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2012 (ኢዜአ) በምዕራብ ኦሮሚያ የተወሰኑ ዞኖች ተቋርጦ የነበረው የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ከዛሬ ጀምሮ ዳግም እንዲጀምር መወሰኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።

መንግስት ከዚህ በኋላ ማንኛውንም ስርዓት አልበኝነት እንደማይታገስና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የክልሉ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል።


የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በተለይም በምዕራብና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቷ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በመንግስት የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አውስተዋል።

በዚህም በተለያየ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አገር ውስጥ ገብተው በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ዕድል ተመቻችቷል ነው ያሉት።

ይሁን እንጂ ራሱን "ኦነግ ሸኔ በማለት የሚጠራው የታጠቀ ቡድን ከሰላም ይልቅ በምዕራብ ኦሮሚያ ቄለም ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ከፍተኛ ጥፋት ሲፈጽም ቆይቷል" ብለዋል።

በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያም በጉጂና ቦረና አካባቢዎች ይሄው ቡድን በሰላማዊ ሰዎች፣ የመንግስት አመራሮች፣ ሠራተኞችና ባለሃብቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።

''ቡድኑ ከቀበሌ እስከ ዞን የተዘረጋውን የመንግስት መወቅር አፍርሷል፣ የፓሊስ ጣቢያና ፍርድ ቤቶችን ሥራ አስቁሟል፣ ባንኮችንም ዘርፏል'' ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

ታጣቂ ቡድኑ ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ከመግደልና ከማሰቃየት ባለፈም መሰረተ ልማቶችን በማውደም የልማት ሥራዎችን ሲያስተጓጉል መቆየቱን አብራርተዋል።

ቡድኑ የቴሌኮም መሰረተ ልምቶችን ማውደሙን የተናገሩት አቶ ሽመልስ "መንግስትም በአካባቢው ሰላም እንዲመጣ በማሰብ የቴሌኮም አገልግሎትን በጊዜያዊነት አቋርጦ ቆይቷል" ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ ሰሞኑን በወለጋ የተለያዩ ዞኖችን በመጎብኘት ከአካባቢው ማሕበረሰብ ጋር  ውይይት አድርገዋል።

በጉብኝቱና በውይይቱ ወቅት በአካባቢው ሰላም መምጣቱን መረዳታቸውንና ከዛሬ ጀምሮ የቴሌኮም አገልግሎት ዳግም እንዲጀምር መወሰኑን አስረድተዋል።

በቀጣይም መሰል የስርዓት አልበኝነት እንቅስቃሴዎችን የክልሉ መንግስት እንደማይታገስ ገልጸው የሕግ የበላይንትን ለማስከበር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

"የሕግ የበላይነት ሲኖር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በትክክል ይካሄዳሉ፣ ሕዝቡም በአግባቡ ተጠቃሚ ይሆናል" ሲሉም አቶ ሽመልስ ተናግረዋል።

"የክልሉ መንግስት የወለጋ ሕዝብ ፍቅር አዋቂና ሰላም ወዳድ መሆኑን ያምናል" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በአካባቢው የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም