በድሬዳዋ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዲታገድ ተወሰነ

73

ድሬዳዋ መጋቢት 22/2012 (ኢዜአ) በድሬደዋ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲታገድ መወሰኑን የአስተዳደሩ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

የእገዳውን ውሳኔ ያስተላለፈው  የአስተዳደሩ ካቢኔና የኮሮና ቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ኃይል እንደሆነ ተገልጿል።

ውሳኔውን አስመልክተው የአስተዳደሩ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት  ወደ ድሬዳዋ የሚገቡና  የሚወጡ ሀገር አቋራጭና መለስተኛ የትራንስፖርት አገልግሎቶች አይኖሩም።

"በተጨማሪም የከተማው የህዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ ባለሶስት እግር እና የሚኒባስ ታክሲዎች እንዲሁም የእንስሳት መጓጓዣዎች ስራቸውን ያቆማሉ" ብለዋል፡፡

ከጅቡቲም ሆነ ከየትኛውም አቅጣጫ ወደ ድሬዳዋ የሚያስገቡ በሮች ዝግ እንደሚሆኑም አስታውቀዋል፡፡

የቫይረሱ ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር  ከመሰረታዊ የፍጆታ መገበያያዎች በቀር እንደ ታይዋን፣አሸዋና መሰል የገበያ ስፍራዎች መዘጋታቸውንም አመልክተዋል።

"የመሠረታዊ የፍጆታ መገበያያዎችም በጥንቃቄ ስራቸው እንዲያከናውኑ ቁጥጥር ይደረጋል" ብለዋል፡፡

ውሳኔው ከነገ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የሚቀጥል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም