በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል ተብለው ከነበሩት መካከል የ24 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ከቫይረሱ ነጻ ሆነች

63

መጋቢት 21/2012 በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል ተብለው ከተለዩት መካከል የ24 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ከቫይረሱ ነጻ መሆኗን  የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

ዶክተር ሊያ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የኮቪድ-19 በሽታ ቅኝትን ከማጠናከር አኳያ በተለያዩ ሆስፒታሎች በተኝቶ ማከሚያ ያሉ የከፍተኛ አጣዳፊ የመተንፈሻ አካል በሽታ ካለባቸው ሰዎች ላይ ናሙና በመውሰድ የኮሮናቫይረስ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ከተወሰደ ናሙና ውስጥ አንዲት ታካሚ ላይ የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባት በመጀመሪያ የላብራቶሪ ምርመራ መታወቁን መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም ለህብረተሰቡ በተሰጠው መግለጫ እንደተገለጸ አስታውሰዋል።

16ኛዋ ታማሚ የ24 ዓመት ኢትዮጵያዊት እንደሆነች የገለጹት ዶክተር ሊያ፤ ታማሚዋ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክና የበሽታው ምልክት ከታየባቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት እንዳልነበራት ተናግረዋል።

ታማሚዋ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክና የበሽታው ምልክት ከታየባቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት ያልነበራት በመሆኑ በድጋሚ ሶስት ጊዜ በተደረገላት የላብራቶሪ ምርመራ ሶስቱም ውጤት ኔጌቲቭ በመሆኑ በቫይረሱ አለመያዟን ለማረጋገጥ መቻሉን አመልክተዋል።

ይሁንና ታማሚዋ የቆየ ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባት በመሆኑ የህክምና ክትትል እየተደረገላት ይገኛል ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የህክምና ክትትል ሲያደርጉላት የነበሩ የሆስፒታሉ ሰራተኞችና ሌሎች ከነሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው በድምሩ 24 ሰራተኞች ለጥንቃቄ ሲባል በተዘጋጀው ለይቶ ማቆያ ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ነው ዶክተር ሊያ ያስረዱት።

24ቱ ሰራተኞች በሚቀጥሉት ቀናት ወደ ስራ ገበታቸውና ቤተሰቦቻቸው እንደሚመለሱም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም