የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር የሚያስችል አዲስ የዲጂታል መረጃ ስርአት ማስተግበሪያ ስራ ላይ ዋለ

75

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2012(ኢዜአ) ንየኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭት ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ መንግስት ከአጋሮች ጋር በመተባበር አዲስ የዲጂታል መረጃ ስርአት ማስተግበሪያ በማልማት ዛሬ ወደ ሥራ ማስገባቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የዲጂታል መረጃ ሥርዓት ማስተግበሪያው የተዘጋጀው በአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስአይዲ)፣ በቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን እንዲሁም አገር በቀልና በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃደኞች ቡድን የጋራ ትብብር እንደሆነ ተገልጿል።

የማስተግበሪያው አላማ በኢትዮጵያ የኮቪድ-19ን ወረርሽኝ ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት በቴክኖሎጂ መደገፍ እንደሆና የቫይረሱን ወረርሽኝ ቅኝት እና ክትትል አቅም ለማሳደግ እንደሚያስችል ተገልጿል።

የዲጂታል ስርአቱ የለማው ለጤና አስተዳደር መረጃ ስርዓት ማስተግበሪያነት እያገለገለ በሚገኘው የመረጃ ስርአት ላይ እንደሆነ ሚኒስቴሩ አመልክቷል፡፡

በጤና ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስተትዩት የሚመራ የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ የማህበረሰብ ጤና ኃላፊዎችና ፖሊስ አርቃቂዎች በወረርሽኝ ወቅት ትክክለኛውን መረጃ በፍጥነት እንዲያገኙ የሚያስችል የዲጂታል የመረጃ ስርዓትን አዘጋጅተው ዛሬ ሥራ ላይ ማዋላቸው ተገልጿል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩት፤ የዓለም ጤና ድርጅትና የተለያዩ የጤና ባለሙያዎች የወረርሽኙን የስርጭት ፍጥነትና የማህበረሰቡን ተጋላጭነት ለመቀነስ መረጃ ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው።

''አዲስ ስርጭትን በማቆም እና የኮቪድ-19 በሽታ የሚያስከትለዉን አደጋ ለመቀነስ የግልና የጋራ መከላከያ እርምጃዎችን መውሰድም ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ይጠበቃል'' ብለዋል።

የዲጂታል ማስተግበሪያዎቹ በዋነኛነት የቅንጅትና ክትትል ስራን በማቀላጠፍ መረጃዎችን መዝግቦ በመያዝና የተለዩ ተጠርጣሪዎችን ክትትል በማድረግ የጤና ሁኔታቸውን መዝግቦ ለመከታተል እንደሚያስችሉ ገልጸዋል።

የላቦራቶሪ ምርመራዎችን ለመላክና ውጤቱንም ለመቀበል፣ ውጤታቸው የታወቀ ታማሚዎችንና ከነሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ሰዎች በቀላሉ ለመለየት፣ እንዲሁም በዚህ ሁሉ መንገድ የተሰበሰበውን መረጃ አጠናቅሮ በመተንተን በማስረጃ ላይ የተደገፈ ውሳኔ በመስጠት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዙም ነው ዶክተር ሊያ ያብራሩት።

ይህ የዲጂታል መሳሪያ በሌሎች አጋሮች እየለሙ ከሚገኙ ሌሎች ጠቃሚ የዲጂታል ማስተግበሪያዎች ጋር ተቀናጅቶ እንዲሰራ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ''የዲጂታል መረጃ ስርዓቱ አዳዲስ ተጠርጣሪዎችን ለመመዝገብና ለመከታተል፣ የላቦራቶሪ ምርመራ እንዲደረግ ለማመላከት፣ የተረጋገጠ የኮሮና በሽታ ታማሚዎች ህክምና እንዲያገኙ ለማድረግና ውጤታቸውን ለመከታተል ያግዛል'' ብለዋል።

በተጨማሪም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የጥሪ ማዕከል ሰራተኞች፣ የፈጥኖ ደራሽ ቡድን አባላት፣ የጤና መኮንኖች፣ የላቦራቶሪ ቴክኒሻኖችና በሁሉም ደረጃ ያሉ የጤና አስተዳደር ሃላፊዎች ስራቸውን በተሻለ ጥራት እንዲሰሩ እንደሚያስችላቸው አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የዩኤስአይዲ ተልዕኮ ዳይሬክተር ሲን ጆንስ የጤና መረጃ ብቻውን የቫይረሱን ስርጭት ባያቆመውም የጤና ባለሙያዎች የሚያደረጉትን የመከላከል ስራን የማገዝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

''በተለይም የበሽታው ጫና እየጨመረ ከመጣ የጤና ባለሙያዎች የሚያደርጉትን ሁሉን ዓቀፍ የመከላከል ስራ ማገዝ ቅድሚያ የሚሰጠው ስራ ነው'' ብለዋል።

ኮሮናቫይረስን ለመሳሰሉ የማህበረሰብ ጤና አደጋዎች የማይበገር የጤና ስርዓት ለመገንባት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን ማቅረብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መስራት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነም አመልክተዋል።

የቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን ዘውዱ በበኩላቸው ወረርሽኙን በአግባቡ ለመከታተልና ለመግታት ጥራቱን የጠበቀና ወቅታዊ መረጃን ሰብስቦና ተንትኖ መጠቀም ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትና ባለድርሻ አካላት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ሊኖራቸው እንደሚገባና ለዚህም መሳካት ሁሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ የተዘጋጀው የዲጅታል የጤና መረጃ ስርዓት የኢትዮጵያን ሕዝብ ከማገዝ በተጨማሪ የአፍሪካ አገሮች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የተዘጋጀው የዲጂታል ማስተግበሪያ ለታሰበለት ዓላማ እንዲውል የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነታቸውን መግለጻቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ያበለጸገው የኢትዮጵያ የተቀናጀ የኮሮናቫይረስ መከታተያና መቆጣጠሪያ በይነ መረብ ስርዓት መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም ተግባራዊ መሆን መጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም