ግድቡን በ2013 ዓ.ም ወደ ቅድመ ኃይል ማመንጨት ለማስገባት በከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር እየተሰራ ነው... ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ

84

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2012( ኢዜአ)ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በ2013 ዓ.ም ወደ ቅድመ ኃይል ማመንጨት ስራ ለማስገባት በከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር እየተሰራ መሆኑን የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ተናገሩ።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የግድቡን ህልውና የታደጉ ውጤታማ ውሳኔዎች ገቢራዊ መደረጋቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

ኢንጂነር ክፍሌ እንዳሉት፤ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የሃይድሮ መካኒክና ኤሌክትሮ ሰቲል ስትራክርቸር በሚፈለገው ጥራት ባለመገንባቱ የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ ሂደት መጓተቱን አስታውሰዋል።

ለግድቡ ጥራት ሲባል የቁፋሮ ስራው ከታቀደው በላይ መከናወኑም ሌላኛው የግድቡን ስራ ያጓተተ ምክንያት መሆኑንም ተናግረዋል።

''ሜቴክ በሚፈለገው ደረጃ አቅሙ ሳይገነባ ግድብን ያህል ውስብስብ ስራ በብቸኝነት እንዲሰራ መደረጉ የውሳኔ ሰጭነት ድክመትን በግልጽ አሳይቷል'' ነው ያሉት።

በተጨማሪ የኮርፖሬሽኑን ስራ በየጊዜው እየተከታተሉ አቅጣጫ ማስቀመጥ አለመቻልም ሌላኛው የአመራርነት ክፍተት መሆኑንም ተናግረዋል።

እነዚህን ችግሮች ለማስተካካል ባለፉት ሁለት ዓመታት ውጤታማ የሚባል የማሻሻሻያ ስራ ገቢራዊ መደረጉን ገልጸዋል።

በሜቴክ ሲከናወኑ የነበሩ ስራዎች በመስኩ ስመ-ጥር በሆኑ የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ሙሉ ለሙሉ እንዲከናወኑ መደረጉ ትልቅ ለውጥ ማምጣቱንም አውስተዋል።

በእነዚህ ዓመታት በተከናወኑ ስራዎች ለቅድመ ኃይል ማመንጫ የሚሆነው የስቲል ስትራክቸር ስራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን በመጠቆም።

አሁን ባለው ሂደት ግድቡ የቅድመ ኃይል ማመንጨት ስራ በ2013 ዓ.ም እንደሚጀምር አመልክተው፤ ውሃ የመያዝ ስራውም በተያዘለት እቅድ መሰረት እንደሚከናወንም ገልጸዋል።

ነገር ግን ይህ እውን የሚሆነው ከኮሮና ስርጭት ጋር በተያያዘ ከፕሮጀክቱ አቅም በላይ የሆኑ ውጫዊ ምክንያቶች  ካላጋጠሙ መሆኑንም አብራርተዋል።

የፕሮጀክቱ ክትትልና ቁጥጥር ስራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድን ጨምሮ በከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ደረጃ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ኢንጂነር ክፍሌ ተናግረዋል።

ግድቡን በሚመለከት በከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ደረጃ የተዋቀረው ቦርድ በየጊዜው የፕሮጀክቱን ግምገማ እንደሚያደርግም ገልጸው፤ የግምገማ ስራው ከወረቀት ባለፈ በመስክ ምልከታ ተደግፎ እንደሚከናወንም ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ ግንባታ 72 ነጥብ 4 የደረሰ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው 44 ነጥብ 3 አንዲሁም የሃይድሮ ስቲል ስትራክር ስራው 20 በመቶ ደርሷል።

ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ ስኬት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም