የኑሮ ውድነትን ለመከላከል ምርት ቀረበ

113

ደሴ ኢዜአ መጋቢት 21/2012  በደቡብ ወሎ ዞን በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት የግብርና ምርት እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች የምርት አቅርቦት መጀመሩን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 623 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን ከእነዚሁ ውስጥም 15 ነጋዴዎች መታሰራቸው ተገልጿል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ እንድሪስ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አንዳንድ አካባቢዎች የግብርና ምርት እጥረት በማጋጠሙ የዋጋ ጭማሪ ተከስቷል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም በ24ቱም ወረዳዎች ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ገበያውን ከማረጋጋት ባለፈ በህገ ወጦች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እጥረቱን ለመፍታትም ለሸማች ማህበራት 9 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ብድር በማመቻቸት ምርቱ ካለባቸው አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች በማስመጣት እጥረት ወደ አለበት አካባቢ በተመጣጣኝ ዋጋ ማሰራጨት ተጀምሯል፡፡

እስከ አሁን ከዘጠኝ ሺህ ኩንታል በላይ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ገብስና መሰል የግብርና ምርቶች እጥረት ወደ አለባቸው አካባቢዎች ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እየተሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ግብረ ኃይሉ ከህብረተሰቡ ጋር ባደረገው ጥረት በዞኑ የተረጋጋ ገበያ መፍጠር ተችሏል ያሉት ኃላፊው ተጨማሪ የፋብሪካና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ወቅታዊ ሁኔታውን ተከትሎ የዋጋ ጭማሬ ባደረጉና የኑሮ ውድነት እንዲፈጠር ባደረጉ 623 የንግድ ተቋማት ላይም እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

እርምጃ የተወሰደባቸውም በምርቶች ላይ ዋጋ በእጥፍ የጨመሩ፣ ምርት አከማችተው የለም ያሉ፣ ጥራት የጎደለው የሚሸጡና ተገልጋዩንም ማጉላላታቸው በመረጋገጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እርምጃ በሚወሰድበት ወቅትም ከፍተኛ ወንጀል ከመስራታቸውም ባለፈ በግብረ ሃይሉ አባላት ላይ ያልተገባ ባህሪ ባሳዩ 49 ነጋደዎች ላይ ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን ከእነዚሁ ውስጥ 15ቱ ታስረዋል ።

የንግዱ ማህበረሰብ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት አቅመ ደካሞችን በመርዳት፣ በመተጋገዝና በመተባበር ቫይረሱን መከላከል ሲገባ የተስገበገበ ባህሪ ማሳየት ተገቢ አለመሆኑንም ተናግረዋል።

እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ ስለሚቀጥል ህብረተሰቡ ጥቆማ በማድረግና ህገ ወጥነትን በመከላከል ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

በደቡብን ወሎ ዞን ከ46 ሺህ በላይ ነጋዴዎች መኖራቸውንም ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም