በደቡብ ክልል ሀገር አቋራጭ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ታገደ

311

ሀዋሳ ( ኢዜአ ) መጋቢት 21/ 2012፡- የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በደቡብ ክልል የሀገር አቋራጭ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ መታገዱን የክልሉ የኮሮና መከላከያና መቆጣጠሪያ ግብረ ኃይል አስታወቀ።
ግብረ ኃይሉ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የትራንስፖርት እገዳ የተጣለው የበሽታው ስርጭት አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱን አመልክቷል።

በክልሉ የበሽታውን ቁጥጥርና ክትትል በማጠናከር የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ የትራንስፖርት እንቅስቃሴው ከመጋቢት 21/2012ዓ.ም. እኩለ ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ ግብረ ኃይሉ ወስኗል።

የግብረ ኃይሉ አባል፣ የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በዚሁ መግለጫቸው አዲስ አበባን ጨምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ  አካባቢዎች ወደ ደቡብ ክልሉ የትኛውም አካባቢ የሚደረግ የህዝብ ትራንስፖርት ስምሪት መቋረጡን አስታውቀዋል።

በክልሉ ውስጥ ሀገር አቋራጭ ትራንስፖርት በቀን እስከ መቶ ሺህ ህዝብ ዝውውር እንደሚደረግ ያመለከቱት  አቶ ማስረሻ ይህ ደግሞ ለቫይረሱ ስርጭት አስተዋዕኦ ስለሚያደርግ ለመከላከል እገዳው መጣሉን ተናግረዋል።

" በክልላችን ወሰን ውስጥ ተሳፋሪን ሳያራግፉና ሳይጭኑ በተፈቀደላቸው ስምሪት መሰረት ማለፍ ይችላሉ" ብለዋል።

በክልሉ ባሉ ዞኖች መካከልና ከዞን ወደ ወረዳ የሚኖር ማንኛውም የህዝብ ትራንስፖርት ስምሪትም ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ተወስኗል።

በደቡብ ክልል የትኛውም አካባቢ ባለሁለት እግር ሞተር ብስክሌት የሚደረግ እንቅስቃሴ ለመንግስታዊ ስራና ለግል አገልግሎት ከአሽከርካሪው ውጪ መሳፈር ክልክል  መሆኑን ተናግረዋል።

ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚመጡ ተማሪዎችን የሚያመላልስ ትራንስፖርት ስምሪት  በልዩ ሁኔታ እንደሚስተናገድ ተጠቁሟል።

የከተማ ታክሲ አገልግሎትን የመጫን ልካቸው 11 ሰዎች የሆነ ሚኒባሶች ስድስት ፣ ባለሶስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች ሁለት ሰዎችን ብቻ እንዲጭኑ ተወሰኖል።

የመጫን ልካቸው ስምንት ሰው የሆነ "ዳማስ " ሚኒባሶች  አምስት ተሳፋሪን ብቻ እንዲያስተናግዱና ታሪፍን በተመለከተ ከተሳፋሪ ጋር ተነጋግረው መሆን እንዳለበት አቶ ማስረሻ ገልጸዋል።

በሽታውን ለመከላከል የተጣለው የትራንስፖርት ገደብ ውሳኔው ለማስፈጸም ህብረተሰቡና ሌሎች የህግ አስከባሪዎች የበኩላቸውን እንዲወጡም መልዕክታቸውን አሰተላልፈዋል።

የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊና የግብረ ኃይሉ አባል ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን በበኩላቸው  ግብረ ኃይሉ ከዚህ በፊት የተለያዩ ውሳኔዎች ቢያሳልፉም ከተግባራዊነት አንጻር ግን ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በየኃይማኖት ተቋማት አምልኮ ስነስርዓትና ግብይት ስፍራ ርቀትን ከመጠበቅ አንጻር ያለው ክፍተት ጥንቃቄ የጎደለው በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባ አመልክተዋል።

የበሽታው ስርጭት አሳሰቢ በመሆኑ ለመከላከል ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ  እንዳለ ጠቁመው ህብረተሰቡም የሚሰጠውን የባለሙያ ምክርና የግብረ ኃይሉ ውሳኔ ተግባራዊ በማድረግ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ሀዋሳና ሌሎች ከተሞች የሚገቡ መንገደኞችን የሙቀት መጠን የመለካት፣ ገቢና ወጪ ተሽከርካሪዎች ላይ ኬሚካል የመርጨት ስራ እየተካሄደ  መሆኑም ተጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም