የኢጋድ አባል አገራት መሪዎች በኮሮናቫይረስ ዙሪያ በቴክኖሎጂ የታገዘ ስብሰባ ሊያካሂዱ ነው

60

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2012(ኢዜአ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን(ኢጋድ) አባል አገራት መሪዎች ከነገ በስቲያ በኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ምክንያት ተራርቀው በቴክኖሎጂ የታገዘ ስብሰባ እንደሚያደርጉ አስታወቁ።

መሪዎቹ በቫይረሱ የስርጭት ባህሪይ ምክንያት በአካል ተገናኝተው መሰብሰብ ስለማይችሉ በቴክኖሎጂ ታግዘው ውይይት እንደሚያካሄዱ ተገልጿል።

ውይይቱ አባል አገራቱ እየሰፋ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት በትብብርና በተቀናጀ መልኩ ምላሽ መስጠት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑን የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አስታውቀዋል።

የኢጋድ አባል አገራት አንድ ግንባር በመፍጠር ቫይረሱን ለመከላከል እያሳዩት ላለው የትብብር መንፈስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ኢጋድ በስብሰባው የሚወሰኑ ውሳኔዎችን ተፈጻሚ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሆነም አመልክተዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አባል አገራት የኮቪድ-19 ሥርጭት በጋራ ለመግታት መስማማታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከቀናት በፊት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።


ኢጋድ እንደ አንድ ቀጣናዊ አሐድ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት እና የሚያስከትለውን የኢኮኖሚ መሰናክል በውጤታማነት ለመከላከል ቁልፍ የመሪነት ሚናን ለመጫወት እንደሚችል መናገራቸው አይዘነጋም።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ከሱዳኑ አቻቸው አብደላ ሀምዶክ፣ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት መሀመድ አብዱላሂ፣ ከጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ዑመር ጊሌ፣ ከኬኒያው ፕሬዚዳንት ኡኹሩ ኬንያታ እና ከደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ጋር በስልክ ተወያይተዋል።

በነበራቸው የስልክ ውይይትም የኮሮና ቫይረስን ላይ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸው የሚታወስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ከተባበርንና በጋራ ሆነን የቀጣናውን ፍላጎት ለማስጠበቅ አመራሩ ከሠራ፣ የቀጣናዊ ቅንጅት ግባችን አይስተጓጎልም” ማለታቸውም እንዲሁ።

መሪዎቹ ለአዳዲስ እና ፈታኝ ሁኔታዎች ተገቢ ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል፣ በቅርበትና በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም