የአባይ ገባሮች ወግ - ከጣና እስከ ካይሮ ጎዳና

622

ከእንዳሻው ሹሜ (ኢዜአ)

የአፍሪካው የወንዞች ንጉስ 'አባይ’ በዓለማችን ከሁለት በላይ ዜግነት ካላቸው በተፈጥሮ ከነገሱ 260 የወንዝ ተፋሰስ ነገስታት አንዱ ነው። የዚህ ንጉስ ስልጣን ደጋፊዎቹ የሚሾሙትና የሚሽሩት አይደለም። አባይ/ናይል ወንዝ በ11 አገሮች ላይ ይነግስ ዘንድ ለዘመናት የተቀባና ክብር የተቸረው እንጂ። አገሮቹ በዚህ የወንዞች ንጉስ ላይ ያላቸው የውሃ አስተዋጽኦ የተለያየ ቢሆንም ዜግነት መስጠት ላይ ግን ተመሳሳይነት አላቸው። አባይ/ናይል የ11 ተፋሰሱ አገሮች ስጦታ ነው።

ከኢትዮጵያ ተነስቶ ሜዲትራኒያን የሚደርሰው አባይ ከጣና ሐይቅ እስከ ሜዲትራኒያን እስኪዘልቅ ድረስ ለደጋውና ቆላው ውበት ነው። ወንዙ የሚነሳባት ኢትዮጵያ አቋርጧቸው የሚያልፋቸው ሱዳንና ግብጽ ደግሞ ከውበትም በላይ የዘርፈ ብዙ አገልግሎቱ በረከት ተቋዳሽ ናቸው።

ናይል ጉዞውን የሚጀምረው ከኢትዮጵያና ከቡሩንዲ ቢሆንም ፍሬ አፍርቶ የሚገኘው ግን ጉዞውን ሜዲተራኒያን ባህር በመግባት ከማሳረጉ በፊት በግብጽ ምድር ላይ ነው። ግብጽ በአባይ በረከት ከጥንት ስልጣኔዋ ጀምራ አብዛኛውን ገጽታዋን ገንብታለች።

በስልጣኑ ጠያቂ የለበትምና ያሻውን ጠቅሞ ሌላውን ቢዘነጋ ሲዘመርለትእንጂ ሲቃወሙት የማይሰማው ይህ የአፍሪካ ወንዞች አባት የዛሬ ዘጠኝ አመት በተጣለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረት ይበልጥ የዓለም ህዝብ እንዲያውቀው ሆነ። ወንዙ የሁሉም ተፋሰስ አገሮች በረከት ቢሆንም ፍሬውን በማጣጣም ረገድ የአንበሳውን ድርሻ የምትወስደው ግብጽ የኢትዮጵያን እንቅስቃሴ አልወደደችውም።

ወትሮም በሰጥቶ መቀበል፣ በጋራ መልማትና ሌላውን ያለመጉዳት አቋም የምታራምደው ኢትዮጵያ የታችኛው የተፋሰስ አባል አገሮች ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ባለሙያዎች ጋር በመሆን የግድቡ ግንባታ የሚያስከትለው ተጽዕኖ ካለ ጥናት እንዲካሄድ በሩን ክፍት አድርጋለች። ባለሙያዎቹም በተለያየ ጊዜ ባወጡት ሪፖርት ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ ተጽዕኖ እንደማያስከትል አረጋግጠዋል።

ይህንን ሁኔታ ሱዳን በአድናቆት ተቀብላ ለግድቡ ግንባታ ፍጻሜ የበኩሏን እገዛ ማድረግ ስትጀምር፤ ግብጽ በተቃራኒው የግድቡ ግንባታ የሚጓተትበትን ሁኔታ ስትፈጥር ማስተዋል ይቻላል። ከአመታዊ የናይል ወንዝ ግብር 85 በመቶውን የሚሸፍኑት ከኢትዮጵያ የተነሱት ገባሮች መዳረሻቸው ግብጽ ነው።

ገባሮቹ ዛሬም ያለማቋረጥ ከኢትዮጵያ ተራሮች እየፈለቁና እየፈሰሱ የተለመደውን ሜዳና ቁልቁለት በጦፈ ክርክር እየተጨቃጨቁ ቁልቁለቱን ተያይዘውታል። የክርክራቸው መነሻ "ታላቁ ንጉስ አባይ ለተወለደባትና ለነገሰባት አገሩ እየሰራ ነው ወይስ አይደለም" የሚለው ጥያቄ ሲሆን ጉዳዩ ስር የሰደደ መሆኑ ደግሞ ጭቅጭቁን እንዲካረር አድርጎታል።

አንዱ ገባር ወንዝ ከማዶ ሆኖ “ንጉስ አባይ በአለም የተዘመረለት፣ ግርማው የሚያስፈራ በማንነቱ የሚኮራ እኛን ወክሎ እየሰራ ያለ ንጉስ ነው” አለ የያዘውን የግብር አፈርና ግንድ እያገላበጠ።

“የለም የለም ‘ንጉስ አባይ’ በራሱ ማንነት የሚኮራ አይደም፣ ለወለደችው እናቱ አልታዘዛትም፣ አሳድጋ ለንግስ ላበቃችው እናት አገሩ እያገለገለ አይደለም” አለ ቁጣ በተቀላቀለበት ድምፅ ሌላው ገባር ከማዶ እየተምዘገዘገ።

”የንጉሱን ስም በከንቱ ለማጥፋትህ ምክንያትህ ምንድነው?'' ሲል የመጀመሪያው ገባር ድጋሜ ጠየቀ።

“አዎ ይህ ንጉስ በማንነቱ የማይኮራ ስለመሆኑ ማስረጃ አለኝ፣ የመጀመሪያው ምክንያቴ ንጉሱ የእኛ ልጆች እየተራቡ አፈር ጠርገን፣ እንጨት ተሸክመን ስንገብር መልሶ ለኛ መጥቀም ሲችል ድንበር አሻግሮ መጓዝ ከጀመረ ዘመናት አልፈውታል”።

“የምንገብረውን ጉልበታችንንም ቢሆን የእናት አገሩ ልጆች በጨለማ እየኖሩ እየተመለከተ እኛ ባዋጣነው ጉልበት መብራት የሚያመነጨው ግን ከድንበር ወዲያ ማዶ ላሉ ለሌሎች ህዝቦች ነው። አንዳንዴ ሳስበው ንጉሱ የያዙትን ይዘው ከኢትዮጵያ ለመውጣት የሚቸኩሉት እኛ ጋር መብራት ስለሌለ ጨለማውን ፈርተው ይመስለኛል”።

"ይገርማችኋል እኛ የምንኖርባት ኢትዮጵያ ገና 60 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የኤሌክትሪክ ብርሃን የለውም ንጉሱ እንደፈለጉ የሚንደላቀቁበት 'የካይሮ' ከተማ ይቅርና በግብፅ አገር 100 በመቶ የኤሌክትሪክ ሃይል አላቸው አሉ"።

“ይህ ሳይበቃው በእናት አገሬ መሬት ላይ የምኮራበት ስሜ 'ንጉስ አባይ' ነው" እያለ ሲፎክር እንዳልነበር፣ ገና እግሩ ድንበር እንደተሻገረ ነው አሉ 'አባይን' ያህል ትልቅ ስም ቀይሮ ‘ናይል’ ተብሎ የሚጠራው ታዲያ ይህ ስሙን መደበቁ በማንነቱ ባይኮራም አይደል?''

"የለም የለም እኛ ኢትዮጵያዊያን ከድሮ ጀምሮ ሰዎችን መርዳት ባህላችን ነው። በዚያ ላይ ንጉሱ የሁለቱም አገር ዜግነት አላቸው እኮ። ታዲያ እንኳንስ የንጉሱ የአብራክ ክፋይ ለሆኑት ቀርቶ አገርን የደፈረ ምርኮኛ እንኳን ስንቁን አስይዞ ወደመጣበት መላክ ነው ታሪካችን"። 

"ታዲያ ይህ ንጉስ ምን አጠፋ ነው የምትለው? እነዚያ የበረሃ አገር ሰዎች ከኛ የባሰ ደሃ መሆናቸውን ደጋግመው ሲናገሩም ሰምቻለሁ ከንጉሱም የሰማሁትም ይህንኑ ነው። ስለዚህ...“ ብሎ ንግግሩን ሳይጨርስ 

አንዲት ለአምስት አመታት እየተመላለሰች የግብፅን ገዳማት በማስጎብኘት ስራ ላይ ተሰማርታ የነበረች ኢትዮጵያዊት ይህን ክርክር ስትመላለከት ቆይታ በመካከላቸው ገባችና "ስለዚህ ይሄ አይን ያወጣ ውሸት ነው" ብላ ቀጠለች

"ንጉሱ የሁለቱም አገር ዜግነት እንዳላቸው አውቃለሁ ቢሆንም ግን ሁለቱንም አገሮች እኩል እያገለገሉ አይደለም " ግራና ቀኝ ሁሉንም እየቃኘች። 

የግብጽን ታሪካዊ ስፍራዎች በማስጎብኘት የአምስት ዓመታት ልምድ ያላት ቅድስት ዳግማዊ የግብፅን ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች ጠንቅቃ ታውቃለች። የንጉሱን የትውልድ አገር ኢትዮጵያንም ቢሆን ተወልዳ ያደገችበት ባጠቃላይ ከጣና እስከ ካይሮ ጎዳና እውነታውን በአይኗ ያዬች በመሆኗ ስለጉዳዩ ሲወራ ዝምታን አልመረጠችም። 

"እስካሁን የምትሉትን ሁሉ ሰምቻለሁ ግን እውነቱ ይህ ነው። እኔ ግብፅ በቆየሁባቸው አምስት አመታት ውስጥ የገጠሩን ህይወት ጠንቅቄ አውቀዋለሁ ህይወታቸው ጭራሹን ከኢትዮጵያዊያን ጋር አይገናኝም"። ለምሳሌ መብራት ሁሉም አላቸው፣ በእንጨት አያበስሉም፣ በጀርባቸው ውሃ አይሸከሙም።

"በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙዎቹ ተማሪዎች በመብራት ማጥናት አይችሉም፣ የህክምና አገልግሎት ሰጪዎች በመብራት እጦት ምክንያት የተሟላ ላቦራቶሪ የላቸውም። በአጠቃላይ የኢትዮጵያና የግብፅ ህይወት ሰፊ ልዩነት አለው። ስለዚህ ንጉስ አባይ የያዙትን ይዘው ወደ ግብፅ እየበረሩ የሚሄዱት በካይሮ ከተማ ያለውን ህይወት ለማጣጣም እንጂ ካላቸው የኢትዮጵያዊነት ርህራሄ አይደለም" ስትል ስሜት እየተናነቃት ነበር። 

ክርክሩን ከጎን ሆኖ ሲሰማ የቆዬው አርቲስት ፋሲል ግርማ ስሜቱን መቆጣጠር አቅቶት ከቅድስት ጎን በመቆም "ልክ ነው ግብፆች እራሱ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ነገር እንዳላቸው አድርጋ የምትከራከረው ነገር ልክ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ከአፄ ሚንሊክ ጀምሮ የውሃ ችግር አለ"።

"አሁን ስንመጣ ከዚህ መቶ ኪሎሜትር በሚሆን አካባቢ ላይ ውሃና መብራት የለም ታዝናለህ ይሄንን የመሰለ ወንዝ እያለን መጠቀም አልቻልንም። ንጉስ አባይ ይህንን እውነት መካድ የለባቸውም ለአገራቸው ሊሰሩ ይገባል" ሲል ጣልቃ ገብቶ ተናገረ።

ገባሮቹ የቅድስትንና የአርቲስት ፋሲልን ንግግር ሲሰሙ በፀጥታ ቅድስትን ማዳመጥ ጀመሩ።

ቅድስት ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ አኗኗርና ስለ ግብፅ ህይወት አነፃፅራ የህዳሴው ግድብን ጉዳይ ስታስብ አንዳች ስሜት ይሰማታል። ምክንያቱ ደግሞ የዛሬ ዘጠኝ አመት ንጉስ አባይ ለአገራቸው እንዲሰሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆ ብሎ ሲወጣ በግብፆች የደረሰባትን ጫና ስለሚያስታውሳት ነው። በርግጥም የ'ንጉስ አባይ' ጉዳይ በኢትዮጵያ ህዝብ ከተወሰነ በኋላ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ያለውን ውጥረት አባብሶታል።

ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ስታደርግ ግብጽ ደግሞ ከዚህ ቀደም የነበሩ ፍትሃዊነት የጎደላቸው ቀደምት የአባይ ወንዝ ስምምነቶች ዘመናቸውን ሳይዋጁ ይቀጥሉ የሚል አቋም ታንጸባርቃለች።

አባይ ለግብፅ ባገለገለበት ረዥም ዘመን ለሁሉም ግብፃዊያን መብራት፣ መስኖና ሌሎች መሰረተ ልማትን ሲያሟላ የቆየ ነው። አሁን ግን ተጸንሶ ለሚወለድባት ኢትዮጵያ ብርሃን ይሆን ዘንድ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ግስጋሴውን ጀምሯል። በአባይ የሚወለደው ብርሃን ብዙ አይቆይም። መላው ኢትዮጵያውያን ደግሞ ተስፋ ሰንቀው የተባበረ ክንዳቸውን በማሳረፍ አሻራቸውን በጋራ እያሳረፉ ይገኛሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም