ከማንጎ ምርታቸው ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዳልቻሉ የአሶሳ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ

211

አሶሳ ኢዜአ መጋቢት 19 / 2012፡- በገበያ ችግርና ህገ ወጥ ደላሎች ከማንጎ ምርታቸው ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዳልቻሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ወረዳ  አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡
ማንጎ በክልሉ አሶሳ፣ መተከል እና ካማሽ ዞኖች እንዲሁም ማኦኮሞ ልዩ ወረዳ በስፋት ይመረታል፡፡

አርሶ አደር አቶ አስረሰ ፍቅሩ በአሶሳ ወረዳ  የአምባ 14 ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ያላቸው የማንጎ ተክል ዛፎች ዘንድሮ ከፍተኛ  ምርት መያዛቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ የማንጎ ተክልም  የያዘው ብዛት ያለው ምርት መሸከም አቅቶት ቅርንጫፉ መውደቁንም ጠቁመዋል።

ከዚህም አብዛኛው ምርት በአነስተኛ ዋጋ ለአካባቢው ገበያ እንደሚሸጡ ጠቅሰው  የተሻለ ዋጋ  የሚያገኙበት ገበያ በማጣትና በህገ ወጥ ደላሎች ምክንያት ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

በወረዳው የኮምሽጋ 28 ቀበሌ አርሶ አደር እንድሪስ እስማኤ በበኩላቸው ወደ ቀበሌው ለግዥ የሚመጡ ህገ ወጥ ነጋዴዎችም ለምግብነት የደረሰውን ማንጎ ከጥሬው ሳይለዩ ከሰበሰቡ በኋላ ትተው እንደሚሄዱ ተናግረዋል።

"ይህም አርሶ አደሩን እንዳይጠቀም አድርጎታል" ብለዋል፡፡ 

በክልል ግብርና እና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ የሰብል ጥበቃ ባለሙያ አቶ ንጉሴ አሻግሬ የአሶሳ እና አካባቢ ማንጎ ከገጠመው በሽታ ተላቆ ዘንድሮ ከፍተኛ ምርት መያዙን ጠቅሰዋል፡፡

ይህንን ተከትሎ ተክሉ የገጠመውን የቅርንጫፍ መሰበር ችግር ለመፍታት አርሶ አደሮች ተክሉን በባላ እና ሌሎች ዘዴዎች በመደገፍ ከጉዳት ሊከላከሉ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በማንጎው ጤና ላይ የተጀመረው ጥናት መቀጠሉን የተናገሩት ባለሙያው ተክሉ በግንዱ ላይ የገጠመው ችግር ካለ በጥናቱ እንደሚታይ ጠቅሰዋል፡፡

የዛፉን ቅርንጫፍ በማሳሳት ተክል የፀሐይ ብርሃን እንዲያገኝ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው አዲስ የሚፈሉ ችግኞችን በጥንቃቄ በማዘጋጀት የተክሉን መጠበቅ እንደሚገባም  ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው ማንጎ ለማዕካለዊ እና ለውጪ ገበያ ለማቅረብ በክልሉ የሚገኙ የህብረት ሥራ ዩኒየኖች ያለባቸውን የገንዘብ እና ሌሎችም የአቅም ክፍተቶች ለማስተካከል ጥረት መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ህብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ እና ማስፋፊያ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አስካል አልቦሮ ናቸው።

"ዩኒየኖቹ ከኢትፍሩት፣ ከአፍሪካን ጁስ እና ጅቡቲ አትክልት እና ፍራፍሬ ድርጅቶች ጋር ስምምነት እንዲገቡ አድርገናል። በቅርቡ ምርቱን መውሰድ ይጀምራሉ "ብለዋል፡፡

አርሶ አደሩ ምርቱን ለመሠረታዊ ህብረት ሥራ ማህበራት ብቻ በማስረከብ የህገ ወጥ ደላሎች እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፍም ኃላፊዋ አሳስበዋል፡፡

"በምርት አሰባሰብ እና አቀማመጥ ሂደት ያሉት ድክመቶችን ለማረም ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል" ያሉት ኃላፊዋ በየደረጃው የሚገኙ የህብረት ሥራ ማህበራት ባለሙያዎች ባለድርሻ አላትን በማሳተፍ የቀጣይ ዓመት ትኩረት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

በአሶሳ እና አካባቢው ማንጎ ከየካቲት እስከ ሚያዚያ መጨረሻ ያሉ ወራት ተክሉ ምርት የሚሰጥባቸው ወቅቶች እንደሆኑም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም