በትግራይ ክልል የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ መደበኛ ትምህርት በኤፍኤም ሬዲዮ ሊሰጥ ነው

449

መቀሌ (ኢዜአ) መጋቢት 19/2012ዓም. በኮሮና ቫይረስ ስጋት ምክንያት የተቋረጠው መደበኛው የመማር ማስተማር ሂደት በሬድዮና በድረ ገጽ ከሰኛ ጀምሮ እንደሚቀጥል የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው ዛሬ እንደገለፀው የመማር ማስተማር ሂደቱ ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚያጠቃለል ነው ።

የቢሮ ኃላፊ ዶክተር ገብረመስቀል ካሕሳይ  እንደገለጹት ቫይረሱን ለመከላከል የትምህርት ተቋማት መዘጋታቸውን ተከትሎ የተፈጠረው የመማር ማስተማር  መቋረጥ በክልሉ በሚገኙ ስምንት ኤፍ ኤም ሬድዮዎች አማካኝነት ለማስቀጠል ዝግጅት ተጠናቅቋል።

የመማር ማስተማር ሂደቱ ከመጪው ሰኞ  እስከ እሁድ ባለው ጊዜ ለአንድ የትምህርት ዓይነት 20 ደቂቃ በመመደብ እንዲሰጥ ይደረጋል ።

ተማሪዎቹ በአንድ ቀን 6 የትምህርት ዓይነቶች በአጭር ሞገድ የሬድዮ ስርጭት/ኤፍ ኤም ሬድዮ /ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የጊዜ ሰሌዳ መውጣቱን የቢሮ ሀላፊው ገልጸዋል።

ትምህርቱ በክልሉ በሰባት ከተሞች በሚገኙ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች እንደሚሰጥ የቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል ።

የሬድዮ ስርጭቱ የገጠር አከባቢዎችንም የሚያዳርስ መሆኑን በጥናት ተረጋግጧል ያሉት  ዶክተር ገብረመስቀል ለኢንተር ኔት ተደራሽ የሆኑ ተማሪዎች በድረ ገጽ ትምህርታቸውን መከታተል ይችላሉ ብለዋል ።

 በአንደኛ ደረጃ የትምህርት ፕሮግራም አምስት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ፕሮግራም ደግሞ ስድስት የትምህርት ዓይነቶች በሬድዮ ስርጭት እንደሚሰጡ ተገልጿል።

 ወላጆች ልጆቻቸውን ሳይዘናጉ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በማድረግ ያላቸውን ሚና ትልቅ መሆኑን በመገንዘብ የድርሻቸውን እንዲወጡ የቢሮ ኃላፊው ጠይቀዋል።

ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል የሚገኙ ተማሪዎች ደግሞ  በወላጆቻቸውና ወንድሞቻቸው አማካኝነት ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ተብሏል ።

በክልሉ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከአንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን  የሚልቁ ተማሪዎች  ከመደበኛ ትምህርት ውጪ መሆናቸው ይታወቃል።