በምስራቅ ጎጃም በትራክተር የተደገፈ የእርሻ ስራ እየተካሔደ ነው

256

ደብረ ማርቆስ፤18 /07/2012 (ኢዜአ) በምስራቅ ጎጃም ዞን የአርሶ አደሩን የመካናይዜሽን እርሻ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ለመኽር አዝመራ ዝግጅት በትራክተር የማረስና የማለስለስ ስራ መጀመሩን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። 

በምስራቅ ጎጃም ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አበባው እንየው ለኢዜአ እንደተናገሩት በመጪው የመኽር አዝመራ የተሻሻሉ አሰራሮችን በመተግበር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ።

በመኽር አዝመራው 650 ሺህ ሔክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ታቅዶ እስከ አሁን ድረስ 4 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ ለዘር ዝግጁ ሆኗል ።

ከታረሰው መሬት ውስጥ 1ሺህ 500 ሔክታር መሬት በትራክተር የታረሰ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ አምስት ትራክተሮች በእርሻ ስራ ተሰማርተው በማገልገል ላይ ሲሆኑ የአርሶ አደሩ የመካናይዜሽን እርሻ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ በቀጣዩ ሳምንት ተጨማሪ አምስት ትራክተሮች ወደ አካባቢው እንዲገቡ ይደረጋል ነው ያሉት።

300 የደጀን፣ ማቻከልና ደብረኤሊያስ ወረዳ አርሶ አደሮች መሬታቸውን በትራክተር እንዲታረስ ማድረጋቸው የመካናይዜሽን እርሻ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ማሳያ ነው ሲሉ ባለሙያው ተናግረዋል ።

በዞኑ 300 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ለማልማት ከወዲሁ ተለይቶ ወደ ስራ መገባቱንም ባለሙያው አስታውቀዋል።

ከትራክተር ተጠቃሚዎች መካከል የደብረኤሊያስ ወረዳ የጫጎ ቀበሌ አርሶ አደር ታደለ ገላው በሰጡት አስተያየት በቀጣዩ የመኽር አዝመራ የሚያለሙትን 2 ሄክታር መሬት በትራክተር በማሳረስ ጊዜና ጉልበታቸውን መቆጠብ እንደቻሉ ገልፀዋል።

የታረሰውን መሬት ዝናብ መጣል እንደጀመረ በበቆሎና ስንዴ ሰብል ለመሸፈን ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

በማቻከል ወረዳ የአመሰግ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙሉጌታ ያዜ በበኩላቸው ቀደም ሲል በበሬ ለማረስ ዝናብ መጣልን መጠበቅ ግድ ይል እንደነበር አስታውሰው አሁን ትራክተሩን በመጠቀም ያለምንም ችግር ማሳረስ እንደቻሉ ገልፀዋል።

አርሶ አደሩ እንዳሉት የእንስሳት ጉልበትን በመጠቀም በሚያርሱበት ወቅት በቂ ዝናብ ባለማግኘቱ ላይ ላዩን ብቻ ይነካኩት እንደነበር በመግለፅ ለማለስለስም ከሶስት ጊዜ በላይ ማረስ የግድ ይላቸው እንደነበር ነው ያስረዱት።

አሁን ግን በትራክተር አንድ ጊዜ ታርሶ በቂ አፈር መገልበጥና ማለስለስ ስለተቻለ የዘር ጊዜ ብቻ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በምስራቅ ጎጃም ዞን በቀጣዩ የመኽር አዝመራ ከሚለማው መሬት ከ26 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።