ኮሌጆቹ ከ2ሺህ የሚበልጡ መምህራንን አስመረቁ

63
ደብረ ብርሀን/ ፍቼ ሰኔ 23/2010 የደብረብርሃን እና የፍቼ  መምህራን ትምህርት ኮሌጆች በመደበኛና ተከታታይ የትምህርት መርሀ ግብር ያሰለጠኗቸውን ከ2ሺህ የሚበልጡ  እጩ መምህራን ዛሬ አስመረቁ፡፡ የደብረብርሃን መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በ13 የትምህርት መስኮች አሰልጥኖ ካስመረቃቸው 1ሺህ 622  መምህራን መካከል 902 ሴቶች ናቸው፡፡ የኮሌጁ ዲን ወይዘሮ ታለፍ ፍትህአወቅ በወቅቱ እንደገለፁት ተመራቂዎች  የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ብቁ ዜጋ በማፍራት ሂደት የድርሻቸዉን ሊወጡ ይገባል፡፡ የኮሌጁ የቦርድ አባልና የዕለቱ ክብር እንግዳ ዶክተር ተፊሪ አድነው በበኩላቸው "ተመራቂዎች በተማሩበት የሙያ ዘርፍ ተግተዉ በመስራት አገር ተረካቢና በመልካም ስነምግባር የታነፀ ዜጋ ለመፍጠር ሌት ተቀን መስራት ይኖርባቸዋል" ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ ውጤት 3 ነጥብ 63 በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነችው  መምህርት እመቤት ሀብተዮሃንስ በሰጠችው አስተያየት ለውጤቷ መሳካት ከግል ጥረት በተጨማሪ የኮሌጁና የቤተሰቧ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አተናግራለች፡፡ "በተማርኩበት የትምህርት ዘርፍ ብቁና በመልካም ስነምግባር የታነጸ ዜጋ ለማፍራት ሀገራዊና ሙያዊ ግዴታዬን ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ" ብላለች ። ሌላው ተመራቂ መምህር ቻላቸው አበበ በበኩሉ ብቁ ዜጋ በማፍራት ሀገሪቱ  ከድህነትና ሙስና ለመለቀቅ ለጀመረችው የለውጥ ጉዞ ስኬት የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀቱን አስታውቋል ። ኮሌጁ ማሰልጠን ከጀመረበት ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ 53 ሺህ 164 መምህራንን ማስመረቁ ታውቋል። በተመሳሳይ የፍቼ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ለ4ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 399 እጩ መምህራን በዲፕሎማ  አስመርቋል ። ከተመራቂዎቹ መካከል ተሸላሚ የሆነችው ወጣት ስኳሬ አለሙ በሰጠችው አስተያየት በትምህርት ቆይታዋ ያገኘችውን እወቀት በተግባር እንደምታውል ገልፃለች። የራሷንም የህይወት ተሞክሮ  መሰረት በማድረግ   ወጣቶች ራሳቸውን ከድህነትና ኋላቀርት ለማውጣት  እንዲተጉ እንደምታስተምርም ተናግራለች። እጩ መምህር አባይነሽ ደስታ በበኩሏ  በትምህርት ቆይታዋ  የቀሰመችውን  እወቀት ለተማሪዎቿ  በማካፈል የሃገሪቱን የለውጥ ጉዞ  እውን ለማድረግ እንደምትጥር ነው የገለጸችው። እጩ መምህራኑ ሰልጥነው የተመረቁት  በሰውነት ማጎልመሻ ፣በቋንቋ፣በተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ  የትምህርት ዓይነቶች ለሶሰት ዓመታት በተግባርና በንድፈ ሃሳብ የተሰጠውን ትምህርት በማጠናቀቅ መሆኑን የኮሌጁ ዲን አቶ ሰለሞን ኃይለማርያም  በምረቃው ወቅት አስታውቀዋል፡፡ ከተመራቂዎቹ  መካከል 197  የሚሆኑት ሴቶች እንደሆኑም ጠቁመዋል ። ኮሌጁ ስራ ከጀመረበት 2007ዓ.ም አንስቶ እስካሁን  3ሺህ 193 መምህራን ማስረቁም ተመልክቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በስድስት  የትምህርት ዓይነቶች አምስት ሺህ አምስት መቶ   የሚጠጉ እጩ መምህራን እየሰለጠኑ እንደሚገኙም ተጠቅሷል፡፡ በክብር እንግድነት የተገኙት የሰላሌ  ዩኒቨርስቲ  ምክትል ፕሬዝዳንት  አቶ አዱኛ መኮንን   የሰለጠነ የሰው ኃይል በብዛትና በጥራት ለማፍራት ኮሌጁ የጀመረው ጥረት የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከየትምህርት ክፍሉ የላቀ ወጤት ያስመዘገቡ እጩ መምህራን ከእለቱ የክብር እንግዶች  የሜዳልያና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም