የኮሮና ቫይረስ በአጭሩ ካልተገታ የቱሪዝም ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ ሊጎዳው ይችላል … የዘርፉ ባለሞያ

454

መጋቢት 17/2012(ኢዜአ) አለም አቀፍ ወረርሺኝ የሆነው የኮሮና ቫይረስ እስከመጪው መስከረም የማይገታ ከሆነ የቱሪዝም ስራዎችን ሊያዳክም እንደሚችል ቱሪዝም ኢትዮጵያ አስታወቀ።

በቱሪዝም ኢትዮጵያ የማርኬቲንግ ኦፕሬሽን ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ደሳለኝ አበባው ለኢዜአ እንደገለፁት ኮሮና የተከሰተበት በአሁኑ ወቅት ብዙ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ የማይመጡበት ጊዜ በመሆኑ በቱሪዝሙ የከፋ ችግር ውስጥ ባይገባም በሽታውን በአጭሩ መግታት ካልተቻለ ግን በዘርፉ ላይ ጫና ያሳድራል።

በኢትዮጵያ ከ5 መቶ 50 በላይ አስጎብኚ ድርጅቶች እንዳሉ የገለጹት ባለሙያው፤ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከ15 በላይ አስጎብኚ ድርጅቶች የሸጡት የጉዞ ፓኬጅ አንደተሰረዘም ገልጸዋል፡፡

የውጭ ቱሪስቶች በአብዛኛው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት  ለአዲስ አመት መግቢያ ጀምሮ በመሆኑ የኮቪድ 19 በሽታ ጉዳቱ እየቀነሰ የሚሄድ ከሆነ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን እምባዛም አይጎዳውም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቅርብ አመታት ወዲህ በቱሪዝም ዘርፍ እድገት እያሳየች መሆኑን የገለጹት ባለሙያው፤ ባለፈው አመት 9 መቶ 62 ሺህ ጎብኚዎች የነበሩ ሲሆን ከዚህም 4.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል።

 የሀገሪቱን የቱሪዝም ቱሪዝሙን የማስተዋወቁ ስራ በስፋት እየተሰራ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ደሳለኝ ፤ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም እና በአለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ኤግዚቢሽኖች ላይ በመሳተፍ ጎብኚ ለመሳብ እየተሰራ ነው ያሉት፡፡