ተመድ የኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር 2 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ጠየቀ

116

አዲስ አበባ መጋቢት 17/2012 (ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ለኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ አገሮች እንዳይስፋፋ ለመከላከልና ለመቆጣጠር  የ2 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ጠየቀ።

የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝና የዓለም አቀፉ የህጻናት መርጃ ድርጅት(ዩኒሴፍ) ዋና ዳይሬክተር ሚስ ሄነሪታ ፎሬ በጋራ የኮሮናቫይረስ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ እርዳታ እቅድን ትናንት ይፋ አድርገዋል።

የድጋፍ ጥያቄው የቀረበው በኮቪድ-19 ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ አገሮች ያሉ ዜጎችን ከወረርሽኙ ለመጠበቅና ዓለም አቀፍ ስርጭትን ለመግታት እንደሆነ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) በድረ ገጹ አስፍሯል።

ድጋፉ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተደራሽ የማድረግ እቅድ አለው።

ኮሮናቫይረስ በአሁኑ ሰአት በግጭቶች፣ በተፈጥሮ አደጋዎችና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሰብአዊ ቀውስ ውስጥ በሚገኙ አገራት መግባቱም ተገልጿል።

"የኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ እርዳታ እቅድ" በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማትና ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና አጋዥ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተግባራዊ የሚደረግ ነው።

በእቅዱ መሰረት የኮሮናቫይረስን ለመመርመር የሚያስችሉ የላቦራቶሪ መሳሪያዎችንና ሰዎች የሚታከሙባቸውን የህክምና ግብአቶች ለአገሮቹ እንደሚቀርቡ ተገልጿል።

በስደተኛ መጠለያና ሰፈራ ጣቢያዎች ላይ የእጅ መታጠቢያ ጣቢያዎችን የሚሰሩ ሲሆን ሰዎች ራሳቸውንና ሌሎች ከቫይረሱ እንዲጠብቁ የሚያስችል የጤና መረጃ ቅስቀሳዎች ይፋ ይደረጋሉ ተብሏል።

በአፍሪካ፣ እስያና ላቲን አሜሪካ የሰብአዊ እርዳታ ባለሙያዎችና ግብአቶችን በማንቀሳቀስ ይበልጥ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ተደራሽ ለማድረግ ማዕከላትና የአየር ትራንስፖርት መተላለፊዎችን እንደሚገነቡ ኦቻ አስታውቋል።  

የኦቻ ሃላፊ ማርክ ሎውኮክ ''ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን አገሮች ችግሩን በራሳችሁ ተወጡ ማለት ጭካኔ ነው'' ብለዋል።

''በእነዚህ አገሮች ውስጥ ቫይረሱ በነጻነት እንዲሰራጭ ከፈቀድን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አደጋ ውስጥ ይገባሉ'' ያሉት ሃላፊው፤ ኮሮናቫይረስ ድጋሚ በዓለም የመሰራጨት እንድል እንደያገኝ አስጠንቅቀዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል የተጋላጭ አገሮች ዜጎችን መርዳትና መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ኮሮናቫይረስ ለሰብአዊነትና ለዓለም ስጋት መሆኑንና ሁሉም ሰብአዊ ፍጡር ቫይረሱን መዋጋት እንደሚገባው የገለጹት ደግሞ የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉትዬሬዝ ናቸው።

የየአገሮቹ የተናጠል ምላሽ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን መርዳት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የመከላከል አቅም ውስንነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በመሆኑም የሰብአዊነት ሃላፊነትን መወጣት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

  እቅድ" ወደ ትግበራ ለማስገባት ከተመድ የድንገተኛ ምላሽ ፈንድ 60 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚደረግም ተገልጿል።

60 ሚሊዮን ዶላሩ ከፈንዱ ላይ ለአደጋ ምላሽ የወጣ ትልቁ ገንዘብ እንደሆነም ተገልጿል።

በተመድ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል በተዘጋጀው የአገሮች የድጋፍ ፈንድ እስካሁን ከሶስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል።

አገሮች የጤና ዘርፍ ወጪያቸውን ለኮሮናቫይረስ መከላከል ብቻ ካዋሉት ኮሌራ፣ ኩፍኝና የማጅራት ገትር በሽታዎችን እንዲስፋፉ እድል መስጠት በመሆኑ ጥንቃቄ እንዲደረግ ተመድ አስጠንቅቋል።

በተመድ የድንገተኛ ምላሽ ፈንድ ወጪ የሚደረገው ገንዘብ ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች፣ ህጻናት፣ ስደተኞችና ተፈቃናዮች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተነግሯል።

ድጋፉ ሰዎች የምግብ ዋስትናቸው እንዲረጋገጥ፣ የአካልና የአዕምሮ ጤናቸው እንዲጠበቅ እንዲሁም የውሃ፣ የተመጣጠነ ምግብና ንጽህና አገልግሎት ራሳቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ እንደሆነ ተገልጿል።

የዓለም የጤና ድርጅት ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስራዎችን ለማከናወን ይፋ ባደረገው የኮቪድ-19 የድጋፍ ፈንድ እስካሁን ከለጋሾች ከ70 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ማግኘቱን አስታውቋል።

በኮሮናቫይረስ 18 ሺህ 589 ሰዎች መሞታቸውንና 416 ሺህ 686 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም